Cyber Ethiopia.com

News

6 hours ago

CyberEthiopia

በኮሮና ቫይረስ የተያዙ 6 ተጨማሪ ሰዎች ተገኙ

************************

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 24 ሰዓት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 74 ሰዎች ውስጥ ስድስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ።

ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 35 እንዳደረሰው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡት ውስጥ አምስቱ ከአዲስ አበባ ሲሆኑ አንዱ ከድሬዳዋ ነው።

በቫይረሱ የተያዙት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው።

በአዲስ አበባ ከተያዙት ውስጥ ሁለቱ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆን፣ የመጀመሪያው የ35 ዓመት ወንድ መጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከዱባይ የመጣ፣ ሁለተኛው የ30 ዓመት ወንድ በተመሳሳይ ከዱባይ መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም የመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለቱም አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት የገቡ ናቸው።

ሦስተኛው የ28 ዓመት ወንድ፣ አራተኛውም የ56 ዓመት ወንድ፣ አምስተኛው የ30 ዓመት ወንድ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ናቸው።

እነዚህ ሰዎች ያላቸው ግንኙነት እየተጣራ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ስድስተኛዋ የ33 ዓመት ሴት ስትሆን፣ በድሬዳዋ ከተማ ከዚህ በፊት በኮሮና ቫይረስ መያዙ ከተገለጸው ሰው ጋር ግንኙነት የነበራት መሆኗ ታውቋል።
EBC
... See MoreSee Less

View on Facebook

20 hours ago

CyberEthiopia

የአድማስ ሬዲዮው ቴዎድሮስ ዳኜ Tewodros Dagne።
ነብስ ይማር 🙏🏻
... See MoreSee Less

View on Facebook

1 day ago

CyberEthiopia

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ለውጥ የመጣበትን ሁለተኛ አመት አስመልክቶ ያስተላለፉት መልእክት
**************************

ያልፋል አትጠራጠሩ!

ክቡራትና ክቡራን ኢትዮጵያውያን

ውድ የሀገሬ ሕዝቦች

የለውጡን ጉዞ ሁለተኛውን ዓመት የምናከብረው በአንድ በኩል ፈተናና ስጋት በሌላ በኩል የተስፋ ውጋጋን ከፊታችን እየታየን ነው፡፡ ሀገራችን ባለፉት ሁለት ዓመታት በለውጥ ሂደት ያገኘቻቸውን ተስፋዎች ለማፍካት፣ ያጋጠሟትን ሳንካዎች ደግሞ ለማስተካከል እየጣረች ባለችበት ወሳኝ ወቅት መላው ዓለምን በጥቂት ወራት ውስጥ በቁጥጥሩ ስር ያዋለው የማይታየው ጠላት የኮሮና ቫይረስ በእኛም አገር አሻራውን አሳርፏል፡፡ በእስካሁን ጉዞው 200 የሚጠጉ ሀገራትን ያዳረሰው ይህ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችንም ገብቶ 29 ሰዎችን የቫይረሱ ተጠቂ አድርጓል፡፡ ነገ ምን ያህል ዜጎቻችንን እንደሚያጠቃ በእርግጠኝነት ባናውቅም ሁላችንም ተረባርበን በዝቅተኛ ጉዳት እንደምናስቆመው ግን ሙሉ እምነት አለን፡፡

ሀገራችን በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ስታልፍ ይኽ የመጀመሪያዋ አይደለም፤ የመጨረሻዋም ላይሆን ይችላል፡፡ በለውጡ ጉዞ የመጀመሪያው ምዕራፍ ወቅት በሶማሌ ክልል የተነሳውና በመሳሪያም፣ በጭካኔም እስካፍንጫው ታጥቆ የነበረው ሀይል በስልጣን ጥም ታውሮ አጎራባች ክልሎችን ሰላም ከማናጋት አንስቶ ክልሉን እስከመገንጠል የተለጠጠ ፍላጎት የነበረው ሲሆን፤ የለኮሰው እሳት የአፍሪካ ቀንድን እስከመረበሽ ሊደርስ ይችላል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ መፈጠሩ አይካድም፡፡ ያም ሆኖ የለውጡ ዓላማ ኢትዮጵያን በፍትሕ የላቀች፣ በዴሞክራሲ የዳበረች፣ በሰብአዊ መብት ጥበቃ የተመሰገነች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ በሰላምና በደኅንነት የተረጋጋች ሀገር ማድረግ ነበርና ከፈተናው ጎን ለጎን በተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት ያ መጥፎ አጋጣሚ አልፎ እዚህ ደርሰናል፡፡

በተመሳሳይ የታጠቁ ኃይሎች በወለጋ እና በሌሎች የምእራብ ኦሮሚያ ክፍሎች ላይ የጥፋት በትራቸውን አሳርፈው ባንክ እየዘረፉ፣ ሰው እየገደሉ፣ ቤት እያቃጠሉ፣ መንገድ እየዘጉ፣ ትምህርት ቤት እየዘጉ ነዋሪውን እያማረሩ የነበረበት፤ ከገጠር ቀበሌዎች አልፎ እንደ ነቀምት፣ ጊምቢ እና ሻምቦ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ መንግስታዊ መዋቅርን ለማፈራረስ የተንቀሳቀሰበት፤ የእለት ተእለት እንቅስቃሴዎች ያለወታደራዊ አጀብ የሚያስቸግሩበት ጊዜያትን አስተናግደናል፡፡ የለውጥ ጉዞው ይሄንንም መጥፎ ጊዜ አልፎ አሁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታችንን እያጣደፍን፣ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶቻችንን በማጠናቀቅ ተስፋችንን ሳይሆን ሪቫን እየቆረጥን ዛሬ ካለንበት ደርሰናል፡፡

በአንድ ቀን በአማራ ክልል ጠንካራ ጓዶቻችንን በግፍ አጥተን፤ በአዲስ አበባ ተወዳጅ የጦር መሪዎቻችን ተገድለው፤ ውጥረቱ ለድፍን ኢትዮጵያ ተርፎ የነበረበት ጊዜ አልፏል፡፡ እዚህና እዚያ እሳት በተለኮሰ ቁጥር ጥፋተኛው ይህና ያኛው ቡድን ነው እየተባለ፤ በየአካባቢው ሀያና ሰላሳ የታጠቀ ጦር ሠራዊት ያለ እስኪመስል ድረስ በየቦታውና በየጊዜው ሰዎች እየተገደሉ፤ አንድ ሰው አልበቃ ብሎ መንደር በሙሉ በእሳት ይጋይ የነበረበት፤ እልቂቱ በአንድ አካባቢ ሳይወሰን፣ ሁለትና ሦስት ክልሎችን ያነካካበት፤ ዜጎች ኢትዮጵያ ልትበታተን ትችላለች በሚል ስጋት ውስጥ እንዲቆዩ የሆነበት አስጨናቂ ጊዜን ተረማምደናል፡፡ ኃላፊነት በማይሰማቸው ሰዎች ንግግር ወንድም እህቶቻችንን የተቀጠፉበት፤ በትንሽ በትልቁ የህግ የበላይነት ያበቃለት፣ ኢትዮጵያም ያከተመላት እንዲመስል ተደጋጋሚ የጥፋት ርምጃዎች የተካሄዱበት ወቅት አልፎ ከሞላ ጎደል ወደ ሰላማችን ተመልሰናል፡፡

የለውጥ ጉዞው በየጊዜው የሚገጥሙትን ጋሬጣዎች ከመሻገር ባለፈ የተለያዩ የሪፎርም ተግባራትን ለማከናወን የተንቀሳቀሰበት ወሳኝ ወቅትም ነበር፡፡ በዚህም፣ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያችንን መሬት እንዲረግጥ ለማድረግ፤ ንግድን ለማሳለጥ የሚያስችል የዱይንግ ቢዝነስ ማሻሻያን በፍጥነት ለመተግበር፤ ከዓለም የንግድ ድርጅት ጋር ስኬታማ ድርድር ለማካሄድ፤ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የብድርና የርዳታ ተቋማት ጋር ኢኮኖሚውን ለመደገፍ የሚያስችሉ ውጤታማ ስምምነቶችን ለማድረግ ችለናል፡፡ በባንኮች ላይ የነበሩ የአሠራር ጫናዎችን ለማቃለል፣ ለሰብአዊ መብትና ለጋራ ተጠቃሚነት ዕንቅፋት የሆኑ ሕጎችና አሠራሮችን ለማስተካከል፤ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ሳይከሰቱ ለማምከን የሚያስችል አቅማችንን ለማደርጀት፤ ግጭቶችን የሚፈጥሩ ግለሰቦችን በሕግ ጥላ ሥር ለማዋል በሙሉ አቅማችን ተንቀሳቅሰናል፡፡ ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ እያመሩ የነበሩ በዩኒቨርሲቲዎችን ወደ መልካም መማር ማስተማር ሂደት ማምራት የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ፣ ስለ ምርጫ፣ ስለ ሀገራችን ብልጽግና እና ስለ ወደፊቷ ጠንካራ ኢትዮጵያ ማሰብ በጀመርንበት ወቅት እነሆ ሌላ ጋሬጣ ከፊታችን ቆሟል፡፡ ምንም እንኳ ፈተናው የመጣው ለመላው አለም ቢሆንም ከፊታችን የተደቀነውን ችግር ለመጋፈጥ እንደ ቀደሙት ጊዜያት ጉልበታችን ላፍታ ሸብረክ እንደማይል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ ሁሌም እንደምናደርገው ሕዝባችንን አስተባብረንና ዐቅማችንን ደምረን በድል ከተሻገርነው በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ጀመርናቸው ሀገራዊ ሪፎርሞች ፊታችንን እንደምናዞር ጥርጥር የለኝም፡፡

ሀገራዊ ለውጥን በጽኑ መሰረት ላይ የመትከል ትግላችንን ጊዜያዊ ፈተና አይገታውም፡፡ አሁን በዓለም ደረጃ የተከሠተውን ዓይነት ፈተና ወደፊትም ይገጥመን ይሆናል፡፡ “ስለ ነገ በትክክል ለመተንበይ የተሻለው ዘዴ ዛሬ ላይ ሆኖ የወደፊቱን መፍጠር ነው” እንዲሉ ለሚገጥሙን ፈተናዎች የዝግጁነት አቅማችንን እያሳደግን እንቀጥላለን፡፡ ኢትዮጵያን ከፈተናዎች በላይ እንድትሆን አድርገን ለመገንባት የሁላችንም ርብርብ ይጠይቃል፡፡ እስካሁን ባለው ጉዟችን የሀገራችንን ኢኮኖሚ፣ ተቋማቶቿን፣ የፍትሕ ሥርዓቷን፣ ማኅበራዊ ደኅንነቷን፣ የሕግ አስከባሪ አካላትን፣ የጤናና የትምህርት ሥርዓቷን በማጠናከር ፈተናዎችን መቋቋም በሚችሉበት ደረጃ ለማደራጀት ጠንካራ የዐቅም መሠረት መጣል ጀምረናል፡፡ ዐቅም ግንባታ ስትራቴጂያዊ ዕይታን የሚጠይቅ፣ ተከታታይ ስራን የሚፈልግ እና ፈጽሞ የማያቋርጥ ረጅም ሂደት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይኽም ደግሞ እንደኛ ድሀ በሆኑ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ግንባር ቀደም የሆኑትን ጭምር የሚመለከት መሆኑ የሰሞኑ ዓለም አቀፋዊ ፈተና ምስክር ነው፡፡
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንኳን እኛን ጠንካራ የጤና መሠረተ-ልማት የገነቡትን ምዕራብያውያን ምን ያህል እያስጨነቀ እንዳለ ሁላችንም እንገነዘባለን፡፡ በብዙ ሀገራት ትምህርት ቤቶች ከተዘጉ ሰነባብተዋል፡፡ በድንበሮች አካባቢ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ ነው፤ የንግድና ስራ እንቅስቃሴዎችም በከፊል ተቋርጠዋል፡፡

የዶላር ግኝት አለኝታችን የሆነው እና ከሀገራችን አልፎ የአፍሪካችን የኩራት ምንጭ የሆነው አየር መንገዳችን እንቅስቃሴው በከፊል ተገቷል፡፡ የአበባ ኤክስፖርት ንግዳችን የሚያንሰራራበት ጊዜ በውል ባልታወቀ አጣብቂኝ ውስጥ ተቀርቅሯል፡፡ በኤክስፖርት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በፋይናንስ ዘርፎቻችን ላይ የተደቀነው ተግዳሮት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ምንም እንኳ እየገጠመን ያለው ችግር ከዚህ በፊት እንዳየናቸው አደጋዎች የማያልፍ ቢመስልም ማለፉ ግን አይቀርም፡፡ ስለተመኘን ሳይሆን በትብብር ስለምንሰራ ይህ ጊዜ ያልፋል፡፡ ከወዲሁ እውቀታቸውን፣ ሀብታቸውን፣ ጊዜና ጉልበታቸውን በመስጠት የትብብር አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ እያሳዩን ያሉ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡

ውድ የሀገሬ ህዝቦች!

የለውጡን ጉዞ ሁለተኛ ዓመት ስንዘክር ምን ዓይነት ኢትዮጵያ እንገንባ የሚለውን እያሰብን መሆን አለበት፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጠነከረ፤ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ያረጋገጠችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች፤ለኢንቨስትመንት ተመራጭ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ማዕከል የማድረግ ርዕይ በውስጣችን ልንሰንቅ ይገባል፡፡ ሰላሟና ደኅንነቷ የተረጋገጠ፤ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጋር ያገናዘበች፤ በአፍሪካ ለቱሪስቶች ተመራጭ የሆኑ መዳረሻዎች ያሏት፤ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቶቿን በሚገባ ማልማት የምትችል ሀገር መገንባትን ታሳቢ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

ይህችን ብሩህ ተስፋ የሰነቀች ሀገር ተሳክቶላት ለማየት ካለፉት ስሕተቶቻችን እየተማርን፣ ያሉንን ወረቶች ይዘን፤ ከሚያራርቁን ይልቅ ለሚያቀራርቡን ነገሮች ትኩረት እየሰጠን፤ ከትናንት ይልቅ ነገ ላይ እያተኮርን መጓዝ አለብን፡፡ ዓለም ከነገ ጋር ለመወዳደር እየሮጠ ነው፡፡ተወዳድረን ማሸነፍ ከፈለግን መሮጥ ቀርቶ መራመድ፣ መራመድ ቀርቶ መቆም፣ መቆም ቀርቶ መተኛት ለእኛ ፍጹም አያዋጣንም፡፡ ያለችንን ጥቂት ጉልበት ይዘን ሽምጥ ለመፈትለክ መፍጨርጨር ነው ምርጫችን፡፡ ሙሉ ትኩረታችንን ታላቁ ሀገራዊ ዓላማ ላይ አድርገን ከተጓዝን ከወጀቡ ባሻገር በስኬት እንሸለማለን፡፡

በመጨረሻም ቀጣዩ የለውጥ ዘመን ካሳለፍናቸው ሁለት የለውጥ ምዕራፎች የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሀገራችንን ወደሚገባት ምእራፍ እንደምናደርሳት አምናለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁላችን የሥራና ጸሎት ሕብረት ያስፈልጋታል፡፡ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ባሉ የተለያዩ የሀላፊነት እርከኖች፤ ከአርሶና አርብቶ አደር ማህበሮች እስከ ንግድና ኢንቨስትመንት ማዕከላት፤ በተለያየ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ሞያተኞች፤ ልሂቃን፤ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት፤ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፤ በየግንባሩ የተሰለፋችሁ የሠራዊት አባላት፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ይመለከተናል የምትሉ ሁሉ ለሀገራችን ጉልበታችሁን ሳትሰስቱ እንድትሰጧት በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ተባበርን፣ ተደመርን፣ በአንድነት ወቅታዊ ፈተናችንን እንሻገራለን፤ የምንመኛትን፣ የምንጓጓላትን፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን እንገነባለን፡፡ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች፣ መስሪያ ቤቶችና ድንበሮች ይከፈታሉ፤ የተቀዛቀዘ ኢኮኖሚያችን ዳግም ያንሰራራል፡፡ ላልተወሰነ ጊዜ የምናደርገው መራራቅ በመቀራረብ ይተካል፡፡ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ወደነበሩበት ይመለሳሉ፡፡ ሞትም በሕይወት ይሸነፋል፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ

መጋቢት 24/ 2012 ዓ.ም
... See MoreSee Less

View on Facebook

3 days ago

CyberEthiopia

www.facebook.com/623401301020450/posts/3495252403835311/የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የምርጫ 2012 ኦፕሬሽን እቅድ እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ የፈጠረውን ችግር ገምግሞ ያሳለፈው ውሳኔ መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2012 ዓ.ም የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ ለማስፈፀም የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ስራዎች ሲያከናውን ከቆየ በኋላ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫው ነሐሴ 23 ቀን 2012 እንዲካሄድ ተወስኖ ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው የተገለጹ ተግባራትን በተያዘላቸው ጊዜ እያከናወነ ለህዝብ እያሳወቀ እንደቆየ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት በያዝነው መጋቢት ወር እና በሚያዚያ 2012 ዓ.ም መጠናቀቅ ያለባቸው በርካታ ስራዎች አሉ፡፡ መከናወን ካለባቸው ስራዎች ዋና ዋናዎቹ የመራጮች ምዝገባ፤ የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ፤ ስልጠናና ስምሪት፤ የመራጮች ትምህርት፤ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ስርጭት የመሳሰሉት ናቸው፡፡

እነዚህን ስራዎች በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ለማከናወን ቦርዱ ተገቢ ጥረት እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ባለፉት ሳምንታት በሃገራችን እና በአለም ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ አስገድዷል፡፡ ከዚሁ የወረርሽኝ ሥጋት የተነሳ በርካታ ሃገራት ምርጫን ጨምሮ መንግስታዊ እቅዶቻቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡ በሃገራችንም መንግስት ወረርሺኙን ለመከላከል የሰዎች ግንኙነትን የመቀነስ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በመወሰኑ የመንግስት ሰራተኞች አብዛኛውን ስራ ከቤት ሆነው እንዲሰሩ ተደርጓል፡መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ ጥብቅ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በክልል መንግስት መስተዳድሮች ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የውስጥና የአገር አቋራጭ የትራንስፓርት ገደቦች፣ የመሰብሰብ ገደቦችን የመሳሰሉ ጥብቅ ክልከላዎች ይፋ ሆነዋል፡፡

በመንግስት ከተላለፉ የክልከላ ውሳኔዎች በተጨማሪ ለቦርዱ ድጋፍ የሚያደርጉ አለምአቀፍ አጋር ድርጅቶች አብዛኞቹ ሰራተኞቻቸው ከቤት ሆነው እንዲሰሩ ሲደረጉ አንዳንዶቹ ደግሞ ጥቂቶቹን ብቻ በማስቀረት ሰራተኞቻቸው ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ድምር ሁኔታዎች በሚያዚያ ሊጀመር በታቀደው የመራጮች ምዝገባ እና ተያያዥ የዝግጅት ስራዎች ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሯል፡፡ ከዚህ የሚከተሉት ከችግሩ ማሳያ ከሚሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

•በኢትዮጵያ አየር መንገድ መጋዘን የሚገኙ የምርጫ ቁሳቁሶችን የማሸግ ስራ በሁለት ሳምንት ዘግይቷል፤
•የቀሪ ህትመት ውጤቶች ግዥ በቫይረሱ ምክንያት በተፈጠረ የአቅርቦት ሰንሰለት መደናቀፍ ምክንያት ተጓቷል፤
•ለምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና ቁጥራቸው 1000 /አንድ ሺ/ በላይ የሚሆን አሰልጣኞችን ክክልሎች ወደ አዲስ አበባ በማምጣት የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት አልተቻለም፤
•ለ 150,000 የምርጫ አስፈፃሚዎች በየክልሎቹ መሰጠት ያለበትን ስልጠና መጀመር አልተቻለም፤
•ቦርዱ የሚሰጠው የመራጮች ትምህርት ኮቪድ 19 ቫይረስን አስመልክቶ በሚወጡ የማህበረሰብ ጤና መልእክቶች ሊዋጡ የሚችሉበት እድል ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የቫይረሱ ስጋት በቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ በአጠቃላይ በተለይም በአፋጣኝ መፈጸም ባለባቸው የመራጮች ምዝገባ፤ የምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና፤ የመራጮች ትምህርት ተግባራት አፈፃፀም ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅእኖ አስመልክቶ ቦርዱ ከህግ አውጪው አካል፤ በጉዳዩ ላይ ከሚሰሩ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የማህበረሰብ ጤና ባለሞያዎች፣ ከአለምአቀፍ አጋሮች እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጋር ተመካክሯል፡፡

ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት አብዛኞቹ ፓርቲዎች የችግሩን ግዝፈት እና በምርጫ ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ተገንዝበው ቦርዱ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ተመካክሮ አማራጭ የአፈጻጸም አቅድ ሊኖረው እነደሚገባ መክረዋል፡፡ይሁን እና በዚህ አግባብ የሚወሰደው እርምጃ ችግሩ ከሚጠይቀው በላይ የሆነ መዘናጋት እንዳያመጣ ቦርዱ በወረርሽኙ አፈጻጸማቸው የማይስተጓጎል ስራዎችን እንዲያጠናቅቅ አሳስበዋል፡፡

ቦርዱ ለውሳኔው መሰረት የሚሆነው የዳሰሳ ጥናት በአማካሪ ባለሙያዎቹ ተሰርቶ እንዲቀርብለትም አድርጓል ፡፡ የተፈጠረው አጠቃላይ ሁኔታ ከታቀደው የምርጫ ምዝገባና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ባግባቡ ለመዳሰስ ያስችለው ዘንድ በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ተመስርቶ ቦርዱ ሁለት የቢሆን ሁኔታ ግምቶች (scenarios) ተመልክቷል፡፡

የመጀመሪያው የቢሆን ሁኔታ ግምት መሰረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት በኢትዮጵያ መንግስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለአራት ሳምንት ብቻ ማለትም እስከ ሚያዚያ 7 ሊቆይ ይችላል በሚል ግምት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ክልከላው የአራት ሳምንት ብቻ የሚቆይ ከሆነ አሁን ባለው የጊዜ ሰሌዳ ዋና የሆነውን የመራጮች ምዝገባ ቢያንስ በአራት ሳምንት የሚገፋው ሲሆን ምዝገባው ቢከናወን የማህበረሰቡ ተሳትፎ፣ የምርጫው ተአማኒነት ማግኘትን እና የኦፕሬሽን ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት ድጋፍን ሙሉ ለሙሉ ማግኘትን በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ያሳያል፡፡

ቫይረሱ በቁጥጥር ስር ካልዋለም የመራጮች ምዝገባን ማካሄድ የማህበረሰብ ደህንነትን አደጋ ውስጥ የሚጥል ከመሆኑም በተጨማሪ ከማህበረሰብ የጤና ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር ጥቂት እንኳን ክልከላዎች የሚኖሩ ከሆነ ይህንን እቅድ ወደ ተግባር መለወጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

በተጨማሪም በያዝነው ሳምንት መንግስት ተጨማሪ እርምጃ እየወሰደ መቀጠሉ ፣እንዲሁም ቦርዱ ከጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ባደረገው ውይይት እስከ ሚያዚያ መጨረሻም ሁኔታው የመሻሻል ዕድል እንደሌለ የተገለጸለት በመሆኑ፣ በዚህ የቢሆን ሁኔታ ግምት በታየው መልኩ የመራጮች ምዝገባን በተያዘለት ጊዜ ማከናወን እንደማይቻል ቦርዱ መረዳት ችሏል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ ሁለተኛ የቢሆን ሁኔታ ግምት የሚያሳየው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ከሚያዚያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ ፤ በመሆኑም በመንግስት የሚደረግ ማንኛውም ከአራት ሳምነት የበለጠ ክልከላ ቢኖር ምርጫውን በተያዘለት ህገመንግስታዊ የጊዜ ሰሌዳ ማከናወን እንዳይቻል ያደርገዋል፤ ስለዚህም ወረርሽኙን መቆጣጠር በሚቻል ጊዜ ቦርዱ እቅዶቹ ላይ የተለያዩ ማሻሻያ ሊደርግ ይገባል የሚል ነው፡፡

በመሆኑም ቦርዱ እነዚህን የቢሆን ሁኔታ ግምቶች መርምሮ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ካደረጋቸው ምክከሮች ያገኘውን ግብአት ታሳቢ በማድረግ የሚከተለውን ወስኗል፡፡

1.በተፈጠረው ሁኔታ የተነሳ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫውን ማካሄድ የማይቻለው መሆኑን በመረዳት ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ በሰሌዳው መሰረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ ወስኗል ፤

2.ቦርዱ የወረርሽኙ ሥጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደገና ግምገማ በማድረግ አዲስ የምርጫ ኦፕሬሽን እቅድና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቀሴውን የሚያስጀምር ይሆናል፤

3.ቦርዱ ባደረጋቸው ምክክሮችና የዳሰሳ ጥናት ላይ በግልጽ የተለዩ፣ በኮቪድ 19 የማይስተጓጎሉ፣ የቦርዱን የምርጫ አፈጻጸም ዝግጁነት የሚጨምሩ፣ሁኔታው ተቀይሮ ተቋሙ ወደ መደበኛ ተግባሩ ሲመለስ በተገቢው ሁኔታ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያሥችል ሁኔታን የሚፈጥሩ ተግባራትን እያከናወነ መቆየት እንዳለበት ወስኗል፡፡

4. በህገ መንግስቱ በተቀመጠው መሰረት በስራ ላይ የሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ጊዜው ከሚያበቃበት አንድ ወር አስቀድሞ ቦርዱ አጠቃላይ ምርጫውን ማድረግ የማይችል መሆኑን ም/ቤቱ ተገንዝቦ፣ ከዚህ አንጻር የሚሰጠው ውሳኔ ቢኖር ለመነሻነት ያገለግለው ዘንድ ይህ ውሳኔ እንዲሁም ቦርዱ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ሰነድ ለህዝብ ተወካዮች እንዲተላለፍለት ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም
... See MoreSee Less

View on Facebook

3 days ago

CyberEthiopia

Breaking news!

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫውን ማካሄድ የማይቻለው መሆኑን ገልፆ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ በሰሌዳው መሰረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ ወስኗል ብሏል።

Source: Elias Meseret
... See MoreSee Less

View on Facebook