ሁሉም መንገድ ፍራንክፈርት ያደርሳል!

ምሥጢረ  ኃይለ ሥላሴ (Click here for the pdf version)

የአውርፓ የባህልና የስፖርት ፌደሬሽን የሚያዘጋጀውና በናፍቆት የሚጠበቀው 13ኛው የእግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ. ከጁላይ 15-18 በፍራንክፈርት/ጀርመን ይደረጋል። ውድድሩ በዚህ መልኩ በፌደሬሽን ታቅፎ ሲዘጋጅ 13 ዓመታት ይቆጠሩ እንጂ ቀደም ብሎ በተወሰኑ ከተማዎችና አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ቡድኖች  መካከል በየሀገሩ በተለይም ጀርመን፣ ሆላንድና እንግሊዝም ይደረግ እንደነበር ይታወሳል። ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ግን በቡድኖች መካከል በእግር ኳስ ጨዋታ ከሚደረገውም ፍልሚያ ባሻገር የኢትዮጵያውያን መገናኛ፣ መተዋወቅያና በተለይም አውሮፓ ለተወለዱ ወጣቶች ኢትዮጵያን በመጠኑም ቢሆን የሚያዩበትና የሚተዋወቁበት ብቸኛው ማዕከል ሆኗል።

ፌደሬሽኑን የመሠረቱት ወንድሞች አጀማመራቸው  በኳስ ተጨዋችነታቸው ዘመን በቅርብ የሚተዋወቁ እየተገናኙ ለመጋጠም ሲሆን እያደር ዐላማው በይዘትም በመልክአ ምድር አቀማመጥም ሰፍቶ ዛሬ ላይ ተደርሷል። አንጋፋዎቹ በወጣቶቹ በተለይም እዚሁ አውሮፓ በተወለዱት እየተተኩ ማየት ጀምረናል።

በባሕል በኩል ይኸን ያህል የሚያመጻድቅ ሥራ ተስርቷል ባይባልም በስፖርቱ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ታይተዋል። ላለፉት ሶስትና አራት ዓመታት በጥቂት ቡድኖች መካከል ሲደረግ የነበረው የወጣቶች እግር ኳስ ውድድር በዘንድሮው የፍራንክፈርቱ  ዝግጅት ላይ ከግማሽ በላይ መጨመሩን የፌደረሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴና የውድድሩ አስተባባሪ አቶ ከበደ ኃይሌ በኩራት ይናገራል። ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ሙሉ ትክረት ተሰጥቶት በስነ-ሥርዓት የተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠብቆ ውድድሮቹ ከዋናው (የ1ኛ ዲቪዚዮንና 2ኛ ዲቪዚዮን)ውድድሮች ጎን ለጎን ይካሄዳል። ይኸ በእንዲህ እንዳለ ላለፉት ዓመታት በተከታታይ ኮከብ ወጣት ተጨዋች ተብሎ የተመረጠው የወጣት ቅዱስ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮ ዙሪክ ቡድን ምንም እንኳ ከወጣቱ ቡድን ሶስቱ ወደ ዋናው ቡድን ቢዘዋወሩም እድሜያቸው 7-10፤ 11-14  የተገነባ ቡድን ይዞ ወደ ፍራንክፈርት እንደሚጓዝ የቡድኑ መሪ ቴዲ ተ.ጊዮርጊስ ገልጿል። በነገራችን ላይ የ13 ዓመቱ ቅዱስ «Football for Friendship» በሚል መጠርያ በ24 አገር ተወካይ ወጣቶች መካከል በርሊን/ጀርመን ላይ የባርስሎናና ጁቬንቱሰ ሻምፕዮንስ ሊግ ግጥሚያ በፊት በተደረገው ውድድር ለስዊዘርላንድ ተመርጦ ከመጫወቱም በላይ ለዋንጫው ፍልሚያ አልፎ 2ተኛ የወጣው የ FC Zurich  አካዳሚ ተጨዋች ነው። በዚህ ለሦስተኛ ጊዜ በተዘጋጀው ውድድር ላይ እያንዳንዱ ክለብ የመጣበት ሀገር ተወካይ በመሆኑ በዚህ ዓመት እንግሊዝን የወከለው የቼልሲ የሴቶች ቡድን በዙሪኮቹ 23-1 አሰቃቂ ሽንፈት ገጥሞታል። ቅዱስ 8 ጎሎችን ሲያስቆጥር 7 አመቻችቶ በማቅረብ በ15ቱ ጎሎች እግሩ አለበት!  የውድድሩ የክብር አምባሰደር ከሆነው ከቀድሞው የጀርመን ኮከብ ተጫዋችና አምበል ተጫዋችም አሰልጣኝም ሆኖ ለሀገሩ ለጀርመን  የዓለም ዋንጫን በተደጋጋሚ ያስገኘው፤ጀርመኖች  „ካይዘር“ ወይም ንጉሠ ነገሥት ብለው ከሚጠሩት ፍራንስ ቤከንባወር በቡድን የብር ሜዳልያ ተሸልሟል ቅዱስ።

qdus
ቅዱስ ከግራ ወደ ቀኝ በፍራንዝ ቤከንባወር ስር ቁጭ ካሉት 4ተኛው፤

 በ13ኛው የፍራንክፈርቱ ውድድር ካለፉት ዝግጅቶች ምን የተለየ ነገር አለ?

በዚህ ዓመት በ1ኛ ዲቪዚዮን 18 ብድኖች በአራት ምድብ በ2ኛ ዲቪዚዮን 12 ብድኖች በ2 ምድብ ይወዳደራሉ (ሰንጠረዦቹን ይመልከቱ) ለመጀመርያ ጊዜ ልምድና ሙያዊ ብቃት ያላቸው 9 ኢትዮጵያውያን ዳኞች ውድድሮቹን እንዲመሩ ተመድበዋል፤ ይኸ ብዙውን ጊዜ ከዳኞች ጋር በቋንቋ አለመግባባት ምክንያት የሚፈጠሩ  አላስፈላጊ ውጥረቶችን እንደሚቀንሰው አቶ ከበደ መሻሻል ተደርገዋል ከሚላቸው ነጥቦች ጎን የሚደመረው ነው። አዳዲስ ቡድኖች ፌደሬሽኑን መቀላቀላቸው እሰየው ቢያሰኝም ሳይንዛዛና በተለይም እያንዳንዱ ቡድን በተመደበበት ሜዳና ሰዐት ተጨዋቾቹን አዘጋጅቶ መቅረብ እንዳለበት አስገንዝቦ ማስፈጸሙ ለፌደረሽኑ ቀላል የሚባል ተግባር አይደለም።

እስካሁን ብዙዎቹ በሀገር ቤት ተጨዋች የነበሩ በየሚኖሩባቸው ሀገሮች ቡድኖች ውስጥ ገብተው ተጫውተዋል እየተጫወቱም ነው። አሁን አሁን እዚሁ አዎሮፓ የተወለዱ ወጣቶች ቡድኖቹን እየተቀላቀሉ በመሆኑ ተጨዋቾችን ከኢትዮጵያ ማምጣትና ቡድን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን እነዚህ ወጣቶች ለሀገራቸው ብሔራዊ ቡድን እስከ መጫወትና የሀገራቸውን ስም ማስጠራት ይችላሉ የሚል ትልቅ ተስፋ በአንዳንዶቹ ላይ እየታየ ነው። ከእነዚህ ታዳጊዎች አንዱ የቅዱስ ታላቅ ወንደም የሆነውና የ16 ዓመቱ ማረን ኃይለ ሥላሴ ለ FC Zurich  U17 ተጫዋች ሲሆን ፍራንክፈርት ውድድር ላይ ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።  ቀስ በቀስ ብዙ ጌድዮን ዘላለሞች ይኖሩናል ለዚያውም ለኢትዮጵያ የሚጫወቱ!

የተወዳዳሪ ቡድኖች ቁጥር ሲጨምር የወጣቶቹም ቁጥር ያድጋልና ፌደሬሽኑና ተሳታፊ ክለቦች ቡድኖቻቸውን በወጣቶች እንዲገነቡ ሊበረታቱ ይገባል።

የዘንድሮ ተፋላሚዎች እነማናቸው?

Teams የዘንድሮ ተፋላሚዎች
የዘንድሮ ተፋላሚዎች

ከላይ እንደተገለጸው የወጣቶቹ ውድድር ቢኖርመ ምድቡ ገና ይፋ  አልሆነም። እንደተለመደው የሩጫ ውድድርና የሴቶች የመረብ ኳስ ውድድር አንደሚኖር አቶ ከበደ ገልጿል።

ቡድኖቹ ሁሉ ፍራንክፈርት መጣንልሽ ሲሉ ፍራንክፈርቶቹ ተዘጋጅተናል በመኪና በባቡር በኣየርም ብትፈልጉ መንገዱ ሁሉ ፍራንክፈርት ያደርሳል እያሉ ነው።

ከመክፈቻው ጀምሮ ያለውን ወቅታዊ ውጤት ጭምር ለ ethiosports.com  ተከታታዮች ለማቅረብ እንሞክራለን

ምሥጢረ  ኃይለ ሥላሴ