ፉክክር፣ ብሔረተኛነትና ትብብር በለውጡ ዋዜማ (ዩሱፍ ያሲን)

በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ቀጣይነት ሊኖረው የሚችል ሁኔታ አይደለም (Unsustainable) ሲባል ሰንበትበት ብሏል። አንድ ሓሙስ ቀረው እየተባለ መነገር የጀመረው ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። የሥርዓቱ እድሜ ካንድ ሓሙስ ይልቅ ከላይ ወደ ዜሮ በሚደረግ የኋሊት መቁጠር የሚዳዳቸው ታዛቢዎቹም አሉ። በፈረንጅኛው Count Down የሚሉት ስሌት መሆኑ ነው። እንደ ተለመደው ኢትዮጵያ ታሪካዊ መጋጠሚያ ላይ ቆማለች፣ በመንታ መንገድ ላይ ናት መባሉ እንደገና እየተዘወተረ መጥቷል። ሁሉም ግን ኢትዮጵያ ወዴት? የሚለውን ጥያቄ እያስጨነቀው ነው። ኢትዮጵያ አሁንም ታሪካዊ መጋጠሚያ ላይ መቆሟ አያነጋግርም። ወያኔ/ኢሕአዴግ አንድ ሓሙስ ቀርቷታል ትንበያ ላይ ሁላችን ባንስማማም በለውጥ ዋዜማ ላይ ናት መባሉ ያስኬዳል። “በለውጥ ማዕበል ዋዜማ ላይ መገኘቷ ሁሉን ቢያስማማም የጉዞዋ አቅጣጫ ወዴት እንደሆነ ግን አነጋጋሪ ይሆናል። አገራችን በዲሞክራሲ ለውጥ አቅጣጫ ትከንፋለች ወይስ ፍርስርሷ ወጥቶ ትበታተናለች? ምኞትና ሟርት፣ ተስፋና ስጋት የሚደበላለቅ ቢሆንም መፃኢ እጣ ፋንታዋ ብዙዎችን ስጋት ላይ ጥሏል። የተወሰኑ ዜጎቿን ያስቆዝማል፤ ያሳስባልም።”ይህንን የከተብኩት የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ነው”1 ። ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ ናት መባሉም ትክክል የሚሆነው በሀገሪቷ የሰፈነው ሊቀጥል የሚችል ሁኔታ አይደለም ከሚለው መሠረታዊ ግንዛቤ ነው። ፈረንጆቹ Unsustainable የሚሉት ዓይነት መሆኑ ነው። ወያኔ/ኢሕዴአግ አደርገዋለሁ ያለው ጥልቅ ተሓድሶ ለጊዜው ወደ ጎን አቆይተን በጥልቅ የለውጥ ማዕበል ዋዜማ ላይ ናት መባሉ ያስኬዳል። ልክ እንደ 1974(1966) ። ልክ እንደ 1991 (1983) ።
2. የገዢው ፓርቲና መንግሥት ግብረ መልስ- መካድ እና መገረም
ወያኔ/ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ መነጋቱን ተቀብሏል። ለምን? ምክንያቱ ቀውሱን በኢሕገ መንግሥታዊ በሆነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መልስ ለመስጠትና ለማስተናገድ እየሞከረ ነው። ለዚህ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው፣ ባለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ማስተናገድ ወይም ማስተዳደር የማይቻል አስገዳጅ ሁኔታ በመፈጠሩ ። ባንዳንድ ቋንቋዎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁኔታ ከተለመደ ሕጋዊ አሰራር ውጭ ያፈነገጠ አሰራር የሚጠይቅ ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ነው።