የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብና የፖሊቲካ ድርጅቶች
(የግል አስተያየት)
ባይሳ ዋቅ-ወያ
የሕወሓት ባልታሰበ ቀንና አኳኋን መንበረ ሥልጣኑን ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባንም መልቀቁ ቅጽበታዊ እንጂ ዘላቂ እፎይታ ሊያጎናጽፈን አልቻለም። አዲሱ አመራር ቃል የገባልንና በተግባር የተረጎመውን አንጻራዊ ነጻነትና ሰላም በደንብ ሳናጣጥም “ጥያቄያችን አልተመለሰልንም” የሚል የተቃውሞ ድምጽ ከያቅጣጫው ተሰማ። በሌላ ቡድን መተካታቸው ያናደዳቸው የሕወሓት ኤሊቶች “የዓቢይ መንግሥት ሆን ብሎ የትግራይን ሕዝብ እያጠቃ ነው” ብለው ስሞታ ማቅረብ ጀመሩ። ታምቆ የነበረው “የማንነት” እና “የክልል ምሥረታ ጥያቄ” በየቀኑ ዓቢይ ጉዳይ እየሆነ መጣ። እስከ ዛሬም “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያልን በየዋህነት አገራችንን የምንታደጋት መስሎን ለኢትዮጵያ ኅልውና ስንታገል መኖራችን ሕዝባችንን ከመፈናቀል ከመገደልና ከመገለል ስላላዳነ እኛም እንደ ሌሎቹ ብሔሮች በመጀመርያ ደረጃ ለብሔራችን መታገል አለብን” ብለው አዳዲስ የአማራ ብሔር “ተወካይ” ነን ባይ ድርጅቶች ብቅ ብቅ አሉ። ይህ ሁሉ አበቃ ብሎ፣ እነቅማንትና አገውን የመሳሰሉ ሕዝቦችን እንወክላለን የሚሉ ድርጅቶች ደግሞ “ድሮም አማራው በግድ አማሮች ናችሁ ብሎን ነው እንጂ እኛ የራሳችን ቋንቋና ባሕል ያለን የኩሽ ሕዝቦች ነንና የተለየ ማንነታችን ይታወቅልን” ብለው የሌሎች ብሔርተኛ ድርጅቶችን ካምፕ ተቀላቀሉ።