ጻሓፊውን በዚህ email email email መድረስ ይቻላል።yussuf.yassin@gmail.com yussuf.yassin@gmail.com

Ethiopia – ከቁጫ እስከ ኦሮሞ – ማንነትና የማንነት ፖሎቲካ እንደምታና መዘዞቹ – ዩሱፍ ያሲን

Click here for the PDF version in Amharic


የአሜሪካ ድምፅና የዶቼቬሌ አማርኛ ራዲዮ ፕሮግራሞች ላይ የቁጫ ሕዝብ የራሱን ማንነት የመወሰን
ጉዳይ አስመልክቶ ለመንግሥት ጥያቄ ያቀረቡ ሰዎች መታሰራቸው ዜና በቅርቡ ተዘግቦ ሰምተናል። 40
የሚሆኑ የአካባቢ ሽማገሌዎች እነዚህ የተሳሩ ሰዎችን ለማስፈታት አዲስ አባባ ድረሰ መምጣታቸውንም
ተዘግቦዋል። የቮይስ ኦፍ አሜሪካ ባልደረባ ጋዘጤኛ ሰሎሞን ክፍሌ በመዛኙ በማንነት ዙርያና ሳቢያ
የተነሳውን ውዝግብ ርእሰ ጉዳይ ላይ የሽማገሌዎች ወኪል ከተባሉት ጋርም ቃለ ምልልስ
አስደምጦናል።

ቁጫ በደበቡ ኦሞ በጋሞጎፋ ዞን በደቡብ በዲታና ዴራማሎ፣ ከደቡብ-ምዕራብ በዛላ፣በምዕራብ
ከደምባ-ፋ፣ በሰሜን-ምዕራብ በዳውሮ ዞንና ከሰሜን ከወላይታ ዞን የሚትዋሰን አንዲት የደቡብ
ኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ወረዳ ናት። ዋና ከተማውም ሰላምበር ትባላለች፣ ይህንን
የዘገበው ዊኪፒዲያ ነው።

ቃል-ምልልስ የተደረጉት የቁጫ ሕዝብ ወኪል ”የቁጫ ሕዝብ ጋሞ አይደለም፣የቁጫ ሕዝብ ወላይታ
አይደለም፣ የቁጫ ሕዝብ ቁጫ ነው ፣ቋንቋውም ቁጨኛ ነው” ነበር ፍርጠም ብለው
ያስረገጡት።በቅርቡ በሶማሌ ክልልም በመሥራቅና በምዕራብ አሚ የሰፈረው የዱቤ ሕዝብ ወኪልም
እንዲሁ “እኛ የዱቤ ብሔረሰብ ሶማሌ አይደለንም፣ ራሳችን የቻልን ሕዝብ” ነን ብሎዋል።የእነሱም
ወኪልም አሁንም በዚያው በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ላይ ቀረበው ነው ይህንኑ ያረጋገጡት።ከዚህ
በፊትም የሥልጤ ብሔረሰብ ”ሥልጤ፣ ሥልጤ እንጂ ጉራጌ አይደለም” የሚል የማንነት ጥያቄ
አነስቶዋል ተብሎ ሪፈረንደም ተፈቅዶለት አብላጫው ”ሥልጤ፣ሥልጤ እንጂ ጉራጌ አይደልም”
ድምዳሚ በድምፁ አፅድቆ እስከዚያ ድረስ በቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ዘንዳ በዘልማድ ከሚታወቅበት
“ጉራጌ” መታወቂያ መለያ የራሱን ማንነት መርጦ ፀደቀለት።ከዚያ በፊት በተለያዩ የኢትዮጵያ
አካባቢዎች አልፎ አልፎ በማንነት ዙሪያ የተነሱ ወይም ለማዕከላዊ መንግሥት ጥያቄ የቀረበበት በርካታ
በማንነት ዙሪያና ሳቢያ የተነሱ ጉዳዮች እናውቃለን።ይህንኑ ማንነት ማጠንጠኛ አድርጎ በወረዳ፣በዞንና
አልፎ ተርፎ በክልሎች መካከል የአከላለል ውዝግቦች ስያናታርኩና ስያወዛግቡ ተመልክተናል።አሁንም
አልፎ ተርፎ ስያገዳድሉም ሰምተናል።

የአሜሪካ ድምፅ የቁጫም ሆነ የዱቤ የማንነት ጥያቄ ዜና እምብዛም የብዙዎቻችን ትኩረት
አልሳበም።የሥልጤ ውሳኔ-ሕዝም ሆነ ውጤቱ ክርክር አላቀጣጠለም ኢትዮጵያውያኑ ዘንድ።ባንፃሩ
ወጣቱ የፖሎቲካ አናሊስት ጆውሃር መሃመድ ከሁለት ሌሎች የኦሮሞ ብሔርተኛ አክቲቪስቶች ጋር
በአለጀዚራም ሰለ ኦሮሞ ማንነት ጥያቄ ዙሪያ ያደረገው ቃለ መጠይቅ ብዙ አቧራ
አስነስቶዋል።አነታርኮዋል።አናቁሯዋል ማለት ይቀላል።

አሁንም በቅርቡ በሚኖሶታ በተደረገው የኦሮሞ የሙስልም ኮሚኒቲ ስብስብ ላይ ይህንኑ ወጣት ምሁር
የኦሮሞ ሕዝብ የመብት ትግል ከኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ትግል ጋር አስተሳስሮ በማቆላለፉ አባባሉ
አንዳንዶቹ እንዳሉት ለኦሮሞ ብሔርተኛ ትግል “መጥለፍ” በመመኮሩ የብዙዎችን ትኩረት
ስቦዋል።አሁንም ብዙ አቧራ አስነስትዋል።ብዙ ውይይትም አቀጣጥሎዋል። በጭሩ ፣ በብዙ
የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ማሕበራዊ መገናኛ ኔትዎርኮች ዘንድ ዓቢይ መነጋገሪያ ርእሰና ሰሞነኛ

አጄንዳ ሆኖ ሰንበቶዋል። መነጋገሪያ ርእስም ሆነ።በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ብዕራቸውን አንስተው
የግራ-ቀኙን ከተቡበት።በሰላ ሂስና ትችት አዥጎዶጎዱበት፣ከየአቅጣጨው።

ለምን ይሆን የቁጫ፣የዱቤ፣የወለኔና ሥልጤ የማንነት ጥያቄ እምብዛም አቧራ ያለነሳው? ባንፃሩ የኦሮሞ
ማንነት ጉዳይ ኢትዮጵያውያንን በጥቅል፣የኢትጵያውያን ብሔርተኞች በተለይ የሚመለከተን? የኦሮሞ
ብሔርተኛነትን የምንፈረው? እነዚህ ርእሰ ጉዳዮች ተመሳሳይነት አልዋቸው።በመሰረቱ ሁሉም
ማጠንጠኛ ያደረጉት የማንነት ጥያቄ ነው።ነገር ግን የዲያስፖራ የኢትዮጵያውያን ለቁጫ፣ለዱቤና
ለሥልጤ ጥያቄና ካአልጀዚራው የኦሮሞ ብሔርተኞች ቃለ ምልልስ የተሰጡት ግብረ-መልሶ ለየቅል
ነበሩ።ለምን? የሚል ጥያቄ ይጭራል።እኔ ጭሮብኛል።ስለ ጫረብኝም ብዕሬን አነሳሁ።እናንተስ?
ለጊዜው ድርጊቶቹና አድራጊዎችን ተግባር ከመኮነን ወደ በስተኋላ ያሉትን የማንነትና የማንነት
ውዝግቦችን ገረፍ አድርጌ ማለፍ መርጥኩ።ትንሽ ታገሱኝ።

ዊኪቢዳያ ሰለ ቁጫ ወርዳ ሕዝብ ምንነትና ማንነት ተጨማሪ መረጃ አለው። 2007 የሕዝብ ቆጠራ
መሰረት ከወረዳው ሕዝብ 98 % ማንነቱን ጋሞ ነው ይላል።አሁንም በተወካዮቹ ምክር ቤት የወረዳው
(የቁጫ?)ተወካዩዋ “እኔ በማንነት ጋሙ ነኝ ብላለች ነው” የተባለው።ይህ ማንነት የሚሉት ነገረ-ጉዳይ
ምን ያህል እንደሚያስቸገር ነው የሚንመለከተው። ለምክር ቤቱ አባል በነጠላ ግለሰብነ ደረጃ ሆነ
ለቁጫ ሕዝብ እንደ ማህበራዊ ስብስብ።ለእኛም እንዲሁ፣ እንደ ሕዝባና ሃገር እያንገላታን ነው።ለምን
ይሁን ይህ “ማንነት” የተሰኘ መለያ መታወቂያ እሴት እንዲሁ የሚያንገበግበን?የ ሚያወዛግበንሳ? አለፎ
ተርፎ የሚያገዳድለን?

የቁጫ ወረዳ ህዝብ ወደ 150 ሺ ህዝብ አለው ይላል።እንቅጩን ለመናገር በ 2007 መሠረት 149,287
ተብሎ ተመዝግቦዋል። በንፅፅር የኦሮሞ ሕዝብ በብሔራዊ የሕዝብ ቆጠራ መሠረት ከሃገሪትዋ ሕዝብ
አንድ ሦስተኛ ነው። የኦሮሞን ብሔርተኛነት የሚንሰጋው በሕዝብ ቁጥር መብዛት ይሁን? የሌላውን
ከቁብ የማንቆጥረው በቁጥር ማነሱ ይሆን? ሁሉም የማንነት ጥያቄዎች ተመሳሳይነት አሏቸው፣
በመሠረተ ሓሳቡ።ሁሉ አንድ ማሕበረስብ መለያ ማታወቂያቸው ዙሪያ ያጠነጠኑ ናቸው ።እርግጥ፣
ኦሮሚያ ከሁሉ ክልሎች የላቀ የመሬት ስፋት አለው። በዚያኑ መጠን ከፍተኛ የሃብት ምንጭ ክምችት
ባለቤት ነው አከባቢው፣ ያለ ጥርጥር።የኦሮሞ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ የሚያሳስባቸው በዚህ ምክንያት
ይሁን? እንዲያውም ከማሳሰብ አልፎ እንቅልፍ የምያነሳ። የኦሮሞ ብሔርተኖች እንደሚወርፉን
አንዳንዴም Phobia መሰል ምክንያት አልባና የተጋነነ ፍራቻ ዓይነት ስጋት የሚወረን?
መልሱ ባጭሩ፣የቁጫ፣ የዱቤ በፊትም የሥልጤ የማንነት ጥያቄዎች ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ያነሳቸው
ሃገር ገንጥሎ በስብስቡ ስም አዲስ ሃገር የመመሥረት ጥያቄ አይደሉም።የቁጫ ሕዝብ ጥያቄ ጣሪያ
ቢነካ እንኳን በመናኻሪያ ወረዳዬ በገዛ ተወላጆቼ ልተዳደር ነው የሚሆነው።የዱቤ ሕዝብ ከሌሎች
ሶማሌዎች በወኪሉ አማካኝነት የተለየን ነን ቢልም ቅሉ ከሶሜሌ ክልል ውጭና ከኢትዮጵያ ውጭ
አዲስ የዱቤ ሪፓብሊክ እመሰርታለሁ አላልም።የሥልጤ ሕዝብም ሪፈረንደም ”ሥልጤ፣ ሥልጤ እንጂ
ጉራጌ” አይደለም መፈክር አንግቦ ተካሄደ እንጂ ሥልጤ ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚል ብሔርተኛ
ዓላማ አንግቦ አልተነሳም። ይህም በሪፈረንደም ድምፀት በአብላጫ ድምፅ ፀደቀለት።ሥልጤ በደቡብ
ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት አንድ ዞን
ባለቤት ሆነ እንጂ በውሳኔ-ሕዝብ ማግሥት የሥልጤ ሪፓብሊክ አልተመሰረተም።
የቁጫ፣የዱቤና የሥልጤ የማንነት እውቂያ ጥያቄ በሃገር በኢትዮጵያ ደረጃ የነበራቸው እንደምታን
አስመልክተን ነወ እንጂ ለጋሙ ዞን፣ለሶማሌ ክልልና ለጉራጌ ብሔረሰብ ላይ ምንም ዓይነት ጫና
አላሳረፍም ማለት እንዳልሆነ ከወዲሁ ግልፅ መሆን ይኖርበታል።ያስርፋል፣ አሳርፎዋልም።

ሰለዚህ የኦሮሞ ማንነት ጥያቄ የሚያስከትለው ውጤትና መዘዝ ነው የአስፈርነት ምንጩ።ያውም በሃገር ደረጃ፣
ያውም በሃገር ሕልውና ላይ።ሦስቱ ስብስቦች የማንነት ጉዳይ ሳቢያ የወሰኑት ሕይወታቸውን ነው፣
በመዛኙ።የኦሮሞ የራሱን እደል በራስ የመወሰን መብቱ ተግባውራዊ አተገባበር ግን ጦሱ ለብዙዎቻችን
ይተርፋል ነው ስጋቱ፣ ያልተኳኳሉ እውነታን እንነጋገር ከተባለ።ጉዳዩ ከኦሮሞ ብሔርተኞቹ እኩል
ይመለከተናል ነው።ምክንያቱ የእኛም እጣ-ፋንታ ብሎም “ማንነት” ይወሰናል ነው።
የኦሮሞ ብሔርተኞች የእነዚህ ወገኖቻቸውን ተገቢ ስጋት መገንዘብ ሊያስፈልጋቸው ነው።እንዴት?
እንዴት!ማለት ያባት ነው።እዚህ ላይ ልብ በሉልኝ!!በቅድሚያ የስጋት ምንጩ እንደ እንቅስቃሴ፣እንደ
ስሜትና እንደ ኢድዮሊጂ የኦሮሞ ብሔርተኛነት እንጂ የኦሮሞ ተወላጆች ልሆኑ እንደማይችሉ
እናረጋግጥ! ይቺን በቅጡ ያዙልኝ!!።ይህን ያህል ስምምነት በቅድሚያ ከተደራረሰን ቀጥታ ወደ ኦሮሞ
ብሔርተኞች የኦሮሚያ ሪፓብሊክ ምሥረታ አተገባበር እንደምታ ጋር እንዝል።

የኦሮሞ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት ኦሮሞውን የራሱን
የወደፊት እድል ብቻ አይደለም እንደ አንደ ስብስብ የሚወሰነው። የበርካታ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች እጣ
ፋንታም ጭምር እንጂ፣ እግረ-መንገዱን።በምርጫ ካርዱ አማካኝነት ማለቱ ሳይሻል አይቀርም።እድል
ተሰጧቸው በሪፈረንድም ለነፃ ኦሮሚያ ድምፃቸውን በሰጡ እለት ማለቴ ነው። የኢትዮጵያን ካርታ ልብ
ብላችሁ ተመልከቱት።ኦሮሚያ በማሓል ሆነ በሰሜን በኩል አማራ፤ አፋር ትግራይና ቤንሻንጉል
ክልሎች አሉ።በደቡብና በምዕራብ የደቡብ ብሔር፤ ብሔረሰቦና ሕዝቦች ክልልና ጋምቤላ ክልል አለ።
ለነፃ ኦሮሚያ ድምፃቸውን በሰጡ እለት የእነዚህን ሕዝቦችና ክልሎች እድልም ጭምር የ ኦሮሞ መራጭ
ወሰነላቸው ማለት ነው።ከላይ ያሉት አራት ክልሎች ከታች ካሉት ሁለቱ ክልሎች ጋር ቢፈለጉ እንኳን
ባንድ ሃገር በአብሮነት የመኖር እድል ከወዲሁ ተነፈጋቸውና።በኦሮሞ ውሳኔ አማካኝነት።በሌላ አባባል
በደቡብና በምዕራብ ያሉት ኦሮሞ ያልሆኑት ኢትዮጵያውን፣ ሰሜን ካሉት ኢትዮጵያውያኑ ጋር አብሮ
የመኖራቸው ፍላጎት በኦሮሞዎች ድምጽ ብቻ ተወሰነ ማለት ነው።በምሳሌ ላስረዳ። የወላይታው
ሕዝብ ከአማራና አፋር ባንድነት ተጠቃልለው የሚኖሩበት መንግሥት መመሥረት ቢመኝ
አይቻለውም።የኦሮሞ ሪፓብሊክ ምሥርታ ኢትዮጵያን በሁለት ይከፍላልና።ለማቃለል ሰሜንና
ደቡብ።ደቡብ ያሉት ብሔረሰቦች ሰሜን ካሉት ጋር በግዛታዊ አንደነት ለመኖር የነበራቸው ፍላጎት መና
ሆኖ ይቀራል ማለት ነው። ምክንያቱም በመሓል ኦሮሚያ የሚባል አዲሱ ሪፓብሊክ ሃገሪቷን በሁለት
የገመሰ አሃድ ተመሥረቶዋልና።በሌላ በኩል ያልመከሩበትን ውሳኔ አለመቀበል ደግሞ መብታቸው
ነው።አለመቀበል ብቻ ሳይሆን አሻፈረኝ ብለው ተግባራዊነቱን ለመቃወም ብሎም ወድቅ ለማድረግ
ለአፀፋ መልስ መንቀሳቀሱ መብታቸው የተጠበቀ ነው።በዚህ ምክንያት በእነዚህ ስብስቦችና በኦሮሞ
ብሔርተኛ ሃይል መካከል ውዝግብ ተፈጠረ ማለት ነው ። ተከትሎ በዚህ ሳቢያ የሚቀጣጠለው
የማያባራ መቆራቆስ ነው የስጋቱ ምንጭ። ይህው የውዝግብ መነሻው ሆኖ ያተረምምሰናል ተብሎ
የሚያስፈራው፣ በእኔ እምነት።በዚያኑ መጠን፣ ይህው ውዝግብ ራሱ የኦሮሞ ብሔርተኞች መጋፈጥ
ያለባቸው አሳሳቢ ተግዳሮት ነው።በዚች አጭር አርቲክል አማካኝነት ሦስት አስቸጋሪ ንባበ ቃላትን ብቻ
ሳይሆን በመካከላቸው ያለው ትስስር፣ተዛምዶና መቆላለፍም ማፍታታት ሊኖርብኝ ነው። እነሱም
ማንነት፣ ብሔርተኛነትና ውዝግብ የተባሉቱ ናቸው።

እዚህ ላይ በስብስቦች መካከል የውዝግብ መነሻና ምክንያት የሆነውን ብሔርተኛነት ቀረብ ብለን
ከመፈተሻችን በፊት ለመሆኑ ማንነት ምንድነው? ብሔርተኛትስ? ለምንስ ይሆን ሰዎች ወይም
ማህበረሰባዊ ስብስቦች በማንነት ዙሪያና ሳቢያ የሚናቆሩት? ለምንስ ይሆን የዘር (ብሔረሰብ) እና
የሃይማኖት ማንነት ከሌሎች የማንነት መገለጫ ተጋሪዮሾች ይብልጥኑ የሚያወዛግቡን? አልፎ ተርፎ
የሚያገዳድሉን? መባሉ ተገቢ ነው።አንዳንድ ጊዜም ስምኑና ”ምንነቱም ሆነ ማንነቱን ” እንኳን

አጣርተን የማናውቀው ግለሰብ “በማንነቱ” ብቻ የምንገድለው?። ሌላው ጥያቄ ሳይቀርብለት ግለሰቡ
በቡድን አባልነቱ ብቻ ታድኖ ለቅጥለት የሚዳርግበት “የማንነት” ቅራኔው ፅንፍ በመርገጡ የሚፈንዳ
ቅጥለት “በማንነት” ተሰኝቶ አገዳዳይ ማንነት ወደ ጅምላ ፍጅት የሚሸጋገርበት አስከፊው እርከን ነው።
በሩዋንዳም ሆነ በቀድሟ ዮጎስላቪያ የታየው ይህው “እንስሳዊ” የሆነ የሰው ልጆች የስሜቶች ሓድራ
እርቃኑን የሚያሳይ ተራደጂ።

ከመቀፅበት ጎሮቤቶች አይገዳደሉም፣ መቼም።እዚህ ላይ ለብዙ ጊዜ ሲንታካተኩ የከረሙ
አለመግባባቶች ናቸው ውዝግቡ ሲሟሟቅ ተጭሮ የሚፈነዱት።አንዱ ስብስብ ሰለሌላው በልቡ ጓዳ
ያስቀመጣቸውን ጭራቅ አሳሳሎች ጠብ ለመጫርም ሆነ ከተጫረ ወዲህም ለማጋጋሉ የሚኖራቸው
ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አንዱ ስብስብ የሌላውን ስብእና የማንጓጠጥ፤ የማንቋሸሽ፤ክፉ
የማሰኘት፤ጭራቅ አድርጎ የማቅረብ፤ ማሸጠይን (ሸይጣን ማሰኘት)፤ጦዘው ጦዘው ወደ ቅጥለት
በማንነት ደረጃ የሚያደርሱት አንዱ የሌለኛውን የጣላት ምስል አሳሳል ሂደቶቹን ተረማምደው ነው
ተብሏልና፣ በከስተቱ አጥኚዎች። መጨካከኑ ለአሳቃቂነቱ ገለጭ ቃል እስከ ማጣት የሚደርስበት ሆኔታ
ባንድ ጀንበር አይከሰትም። አንዱን ሌላው ከምደረ-ገፅ ካላስወገደ የራሱን ዓላማ ግብ ማስመታት
አይችልም ወይም የጠላቱ ዓለማ እንዳይሳካ ማድርግ አይችልም ወደሚለው ድምዳሜ መድረሱን
የሚያመለከት አተያይ ነው፣ መቼም።ሁሉም የማንነት ውዝግቦች ወደዚህ ዓይነቱ አገዳዳይ
የማንነት ፍጅት አያመሩም።ቢሆንም ከጥላቻ ቆጠብ እንበል!እባካችሁ።
ለመሆኑ ማንነት ምንድ ነው? ውዝግብስ?ብሔርተኛነትስ?

እንደሚታወቀው ”እነሱ”ና ”እኛ” መባባሉ አዲስ ነገር አይደለም፣ በሰው ልጅ ታሪክ።ገና በሰው ልጅ
ታሪክ ማለዳ የተፈጠረ የአፈራረጅ ዘይቤ ነው። ጎራ ለይተው “እነሱ” እና “እኛ” ተባብለው መቧደኑ
ከጥንቱ ከጧቱ የነበረ ነው ይሉናል የማሕበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች።ማንነት አንዱ ስብስብ ”እነሱ”
ከሚላቸው በተፃረረ አልፎ ተርፎም በተፋጠጠ መልኩ ራሱን የማስቀመጥ (Identify) ክንዋኔ እስከ
ተባለ ድረስ ቢዘገይም ፍጥጫው ወደ ግጭት መመራቱ አይቀሬ ነው የሚመሰለው።ማንነት ሁለት
ማጠንጠኛ አለው።አንደኛው በተመሳሳይነት ላይ የተመሰረተ ተጋርዮሽነትና ዝምድና አባላቱ እንደ
ስብስብ እንዳላቸው ማረጋገጡ ሲሆን፤ሌላኛው ደግሞ ይህንኑ በማረጋገጡ የሚከናወነው ”እነሱ”
ከሚሏቸው በተፃራርነት መሰለፍና መቆሙን መመርኮዣ ያደረገ ክንዋኔ ነው።ከላይ መተመለክናቸው
ምሳሊዎች “ሥልጤ ነኝ ብሎ ማስረገጥ፣ በሌላ በኩል ግን ጉራጌ አለመሆኑን እንዲታወቅለት ማድረግ
ተግባር ነው።”የዱቤ ብሔረሰብ ነኝ እንጂ ሶማሌ አይደለሁም፣”ቁጫ ነኝ ነገር ግን ጎፋም ሆነ ወላይታ
አይደለሁም” ዓይነቱ አካሄድ ይህው ነው።

ማንነት አንድ ማህበረስብ ራሱን በራሱ የሚያስተዋውቅበት ብቻ ሳይሆነ በአካባቢው የሚታወቅበት
መለያ ነው ይሉናል አሁንም የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎቹ። ከሁሉ በላይ ግን ለአባላቱ ጠቃሚና
ወሳኝነት ያለው ፍረጃ ነው።ይህ ፍረጃ አስፈላጊነቱና ትርጉም ሰጭነቱም እዚያ ላይ ነው።
ማንነት (identity) በቀላሉ አማርኛ መለያ ቢባል ይቀላል።ባጭሩ የመለያ መታወቂያ መግለጫ ነው
ቢባል አልቅጥ አቃለላችሁት አንባልም።መለያ መታወቂያነቱ ግን ቡድን ተኮር ነው።ያንድ ስብስብ
ወይም ቡደን በተጋርዮሽነታቸው ላይ የተመሰረተ ትሥሥር አወካከል ነው። symbolic
representation ወይም ተምሳሊታዊ አወካከል ነው እንጂ ጋሃዳዊ አይደሉም ይሉናል አሁንም
ተማራማሪዎቹ። አንድ የመሆናቸው መመሥረቻው ግን ከሌሎቹ ቡድኖች በጋርዮሽነታቸው
የሚለያቸው መለያዎች ላይ ሲመረኮዝ ነው ልዩነቱ ንጥሮ የሚጎላው።የእነሱነታቸው ዋናው መግለጫ
ከሌላው ስብስብ የሚለያቸው እነሱ ለብቻቸው የሚጋሩትንና ከሌላው ጋር የማይጋሩትን ተጋርዮሾች

ናቸው መለያ ምልክቶቹ።ለማፍታታ ሊሞክር መሰለ።ልብ ማለት ያለብን ሌላ ቁም ነገር አለ።ስብስቡ
የቡድን ተጋርዮሹነታቸው በተጨማሪ ሌላ መመሥረቻ አለው።ጋራነታቸው የሚፈጠረው በእነሱ ዘንድ
”እነሱ” የተሰኘ ሌላው ቡደን በተፃረረ አምሳያ አሳሳል ነው።ይህ ደግሞ ዝምድና የመፍጠርና ዝምደና
የመካድ ወህደት ነው፤ ባንድ ላይ።ዝምድናው ወይም ትሥሥሩ የትውልድ ቆጠራና የደምና የተዋስቦ
ቁርኚት አዘማመድና መተሳሰር ብቻ አይደለም።በዚሁ አማኻኝነት መተሳሰሩም እንዳለ እሙን
ነው።እንዲያውም ለዚሁ ዝምድናና ተጋርዮሽ ቁርኚት ቅድሚያ የሚሰጡ አሉ።ያንድ ቅድመ አያት
ልጅነታቸው ዋናውና ወሳኝ ተጋሪዮሽ ሆኖ ይቀርባል ፤በዚህ ዝምድና አመሰራረት።የተጋሪዩሹ ሕትመት
በስጋ ወልደቱ በደም ወህደቱ ትሥሥራቸው የሚቆያራኛቸው።በእኛ ሃገር አፋሮችና ሶማሌዎች
በተወሰነ መልኩ ኦሮሞች በቅድመ አያት የዘር ሓረግ ቆጠራ ጋራነታቸውን ወይም አንድነታቸውን
ያስረግጣሉ።የስጋና የደም ትሥሥርን ያስቀድማሉ ማለት ነው።ቅድሚያ ለዚህ ትሥሥር ይሰጣሉ
ማለት ነው እንጂ ልክ እንደ ሌላው ከሌሎቹ ስብስቦች ፈንጠር በለው በተነፃፀረ አኳኋን የራሳቸውን
ማንነት እያስረግጡም ወይም አፅናኦት አይሰጡም ማለት ግን አይደለም።የተባለው የጋራ ቅድመ
አያትም በዚች ምድር አካል ነስቶ፤ነፈስ ዘርቶ ያልተመላለሰ ተረት ወልድ ፍጡር ሊሆን እንደሚችል
መዘንጋት የለበትም።በዚህም የትሥሥር ዝምድና አመሰራራት የተወሰነ በምናብ የሚበጃጁ አፈጣጠሮች
ሚና አላቸው።ይህም በማንነት ከማያውቋቸው ዘመዶች ጋር በምናብ ዝምድና ተከል ተጋሪዩሽ
ነው።የምናብ አፈጣጠሩ ጉዳይ ማንነትን ወሰብሰብ ያለ ፍረጃ ያደርገዋል።ይህንን የማይታይና
የማይዳሰስ “የእኔነትና የእኛነት፤ የእሱነትና የእነሱነት” ራስ ወገን ለይታና የሌላውን ለይታ መግለጫ ልክ
ታዋቂው አርቲስት ማህሙድ አህመድ ሰለ ፍቅር ረቂቅነት ሲያንጎራጉር ” ፍቅር ፍቅር ይባለል እንጂ
ማንም አላየው ሲሄድ በአካል” እንደሚለው ዓይነት አይዳሰስነት ያለው ክስተት ነው።ከቅድመ አያት
ትሥሥር ላይ የጋራ የሶቆቃ የጋራ ታሪክ፤ ያንድ ሌላ ስብስብ ተፀራሪነት፤—— ወዝተ ይደረባል።
የወደፊት እጣ ፋንታ ቁርኚት ይታከልበታል።ብሔርተኛነት የተሰኘው ርዮተዓላም፤ ስሜትና እንቅስቅሴ
መልክ ተላብሶ ጦር ያማዝዛል።

ውዝግብ
ሰለዚህ ማህበራዊ ስብስቦች በቡደን ቡደን መቧደናቸው አይደለም ወደ ግጭት የሚያመራቸው ተፃራሪ
ወይም በጊዜው ተፃራሪ የሚመስላቸው ግቦችን በየፊናቸው ለመምታት ማለማቸው እንጂ።ይህ
ድርጊት ነው እንግዲህ ውዝግብ የሚሰኘው።የ Conflict ( ውዝግብ ) አጥኚዎች፣ ወዝግብ ” ሁለት
ወይም ከዚያ በለይ የሆኑት ወገኖች ተፃራሪ ሆነው የሚታያቸውን ዓላማዎች አንግበው አንዱ የሌላውን
ዓላማ ግብ መምታት እንዳይይሳካ የማድረግ ክንዋኔ ነው ” ይሉናል። በግለሰቦች መካከል በነጠላ
ማንነታቸው የሚነሱትን አለመግባባቶች ለጊዜው ከዚህ ውጭ እናድርጋቸውና ሌላውን
እንመልከት።ሰዎች ሕወታቸውን ሲመሩ የተለያዩ ግቦች አንገበው እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል። በዚያኑ
መጠን ተፃራሪ የሚመስሉ ፍላጎት ፤ ዓላማ ፤ ጥቅምና አመለካከቶችን ያራምዳሉ።እነዚሁ ሌሎቹ
ካነገቡትና ከሚያራምዱት ሳይጣጣሙና የተቃረኑ ሲመስሏቸው

ይሻኮታሉ፤ይሯኮታሉ፤ይቆራቆሳሉ።ባጭሩ ጠብ ይፈጥራሉ። ባንድ ዓላማና ፍላጎት ተፃርረው ጎራ
ላይተው ሁለቱም የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካትና በዚያኑ መጠን የሌለኛውን ዓለማ ስኬት ለማደናቀፍ
አልፎ ተርፎ ወድቅ ለማድረግ በየፊናቸው ይፍጨረጨራሉ።በዚያኑ ወቅት ዓላማዎቹ ተፃራሪ ሰለሆኑ
ወይም ለግቡ አንጋቢዎች ተፃራሪ ዓላማዎቻቸን ማጣጣም የማይቻል ሆነው ሰለምታዩዋቸው የግድ
ጎራ ይለያሉ።ይፋጠጣሉ።ደረጃው ይለያያል እንጂ ከቤተሰብ አለመግባባት እስከ ሶማሊያው ዓይነቱ
አመሰቃቃይ እርስ በእርስ ጦርነት የመሳሰሉት ቁሩቁሶች ሁላ በውዝግብ ውስጥ ነው የሚጠቃለሉት ፤
ለውዝግብ ተመራማሪዎቹ።ሰለዚህ በቡደን ቡደን መቧደኑ አይደለም ወደ ግጭት የሚያመራቸው
ተፃራሪ ወይም ተፃራሪ የሚመስላቸው ግቦችን ለመምታት ማለማቸው እንጂ።

ያንዳንዱ ስብስብ ራሱን ላይቶ የማስተዋወቁ መነሻው ”እኛ”፤ ”እነሱ” አይደለንም በማለት ራሱን
ከሌሎቹ የሚለይበት መገለጫዎቹ ናቸው ነጥረው የሚወጡት፤ በቅድሚያ።ፍንትው ብለው
የሚታዩን። ዓይን የሚገቡት እነሱ ናቸውና። በሌላ አነጋገር ”እነሱ”ና ”እኛ” መሰኛኘት የጀመርን
እለት ለራሳቸን መለያ መታወቂያ አበጀን ማለት ነው።ራሳችን ከሌላው በመለየት ነው የሌላውን
ማንነት ለይታ ሂደት ”ሀ፤ሁ” ብለን የምንያያዘው።”እኛ” ከከሌላው ለየት አድርጎ በሚያለያየን
ተጋሪዮሽ (Commonness) ላይ ተመስርተን ነው “እነሱ” እኛ ” እኛ” አንድ አይደለንም
የሚያስብለን።ሰለዚህ የጋራ መለያ-መታወቂያ የለንምም የሚያሰኛው።በተጋሪዮሾቹ ዙሪያ
የምንፈጥረው ልዩነትና በአመዛኙ የማይዳሰሱ እሴቶች (Vaules) ስብስብ ወገንተኛነት
የመፍጠሩ ሂደት በሰው ልቦናና በምናብ (Imagination) አማካኝነት ሰለሚከናወን ሂዴቱ
ረቀቅ ይላል።እኔ ለማለት ከፈለኩት በላይ ወሰብሰብ ይላል ማንነት።በነጠላ ግለሰበነትም
በስብስብነት የሚያሥተሳስረውን በርካታ የወገንተኛታቸውን የሚያረጋግጥ ተጋሪዮሻቻቸውን
ይደረደራሉ። በግለሰብም ሆነ በቡድን የአንድ ማሕበራዊ ስብስብ ወገንተኛነት ባመዛኙ ምናብ-
ወለድ ቢሆንም ቅሉ ግለሰቦቹና ቡድኖች እስከ ተቀበሏቸው ድረስ ትርጉም-ሰጪና ወሳኞች
ናቸው ለእነሱ ። ቀላል ክንዋኔ ይመስላል ግን አይደልም።።በግለሰቡ ጭንቅላት የራሱን
ወገንተኛነት በመለየት የሚከናወን ረቀቅ ያለ ሂደት ነው ።”ማንነትም” ይህንን ያህል ለፊቺና
ለትርጉም አሻፈረኝ የሚል የተወሳሰበና የተቆላለፈ እሴትና ርዮተዓለማዊ ፅንሰ ሓሳብ ለመሆን
የሚበቃው በዚህ ምክንያት ይመስለኛል።

ብሔርተኛነትና መዘዞቹ
ብሔርና ብሔርተኛነት የተያያዙ ናቸው ማለቱ ያስኬዳል።አንድ ብሔር አባለት በወገነታኛቸው
ተመርኩዞ የራሱን መንግሥት ወይም መንግሥት መሰል አሓድ የመመሥረት ፍላጎትና ምኞት
ነው ።ይህ ፍላጎትና ምኞት እንደ ስሜት፣እንደ ኢድዮሎጂና እንቅሳቃሴ ባሕርይና መልክ
ተላበስው ከሌሎች መሰል (በባለዙ ብሔር ሃገር?) ስብስቦች ጋር ሲያጋጭ ነው ብሔርተኛነት
የሚሰኘው።ሰለዚህ ብሔርን ከብሔርተኛት ጠንቅ ጋር አስተሳስሬ መመልከቱን ተገቢ
ይመስለኛል።ሰለዚህ ብሔርተኛነት ደግሞ ከብሔር-ጠቅልል መንግሥት ምሥረታ ጋር እስከ
ተቆራኘ ድረስ ብሔርና ብሔረተኛነት የግድ ከመንግሥት ጋር ካላቸው ዝምድና በተያያዘ መልኩ
ነው የሚታዩትም ።በተለም ከብሔራዊ መንግሥታት መሥረታ ጋር።በኤውሮፓ የተመለከትነውም
ይህው ነው።ምናልባት በእኛ ሃገር ከማዕከላዊ መንግሥት ምሥርታው ታሪክና በዚህ ታሪክ ላይ
እስካሁን ባለተገኘ መግባባትን ተመርኩዞ ነው የሚያወዛግበን።

ብሔርተኛነት፤ በርካታ ትርጉምና ፍቺ ሊኖር እንደምችል ባያከራክርም ማኪል ማን የተባለው ፅሓፊ
ብሔርና(nation) ብሔርተኛነት(Nationalism) አያያዙ ” A nation is a community affirming a
distinguished ethnic identity, history and destiny and claiming its own state ባንድ አጭር
ጥቅስ ያፍታታዋል ።ማህበረሰቡ የተወሰኑ ተጋሪዮሾችን ምርኩዝ በማድረግ በታሪክ ሂደት መታነፁና
መርጋቱን ካረጋገጠ በኋላ የራሴን መንግሥት ይገባኛል መብቱን የማስረገጥ ፍላጎቱ ነው ጎልቶ
የሚታየው። ማኪል ማን A Political Theory of Nationalism and its Excesses በተሰኘው
መፅሓፉ ቀጠል አድርጎ ብሔርን ከብሔርተኛት ጋር “Nationalism is an ideology whereby a
nation believes it possesses distinct claim to virtue-claims which may be used to
legitmise aggressive action against other nations” በማለት በጥብቅ ያቆራኛቸዋል።

ብሔርተኛነት ባንዱ ስብስብ ሌላውን በጥሬጣሬ፣ በንቀትና በጥላቻ መመለከቱ ጉዳይ ብቻ
አድርጉ መመልከቱ የተወሰነ እውነተኛነት ቢኖርውም ቅሉ ሙሉን ሥዕል አይፈነጥቅም።
ብሔርተኛነት አንዱ ብሔር የራሱን መንግሥት ሊኖረው እንደሚገባ የሚያነሳው ጥያቄ ነው
የሚተለዋ የፃሓፊው አጭር አባባል ማለፊያ መግቢያ ናት። በዚህ ፅሑፍ በዚህ አግባብ ነው
የሚጠቀምበት::ሁለተኛው ደግሞ ይህንን የራሴ መንግሥት ይገባኛል ፍላጎት የሚፃረሩትን ሌሎች
ብሔሮች አንፃር ጠላትነት ስሜት ማኮተኮት እንደ ትክክለኛ መስተጋቢርና መብቱ አድርጎ
ሲመለከት ነው ግንኑኝነቱ መዛባት የሚጀረው። ብሔሩ የራሴ መንግሥት ያስፈልግኛል በማለቱ
ሳቢያ በስብስቦቹ መካከል ግንኑኝነቱ ሊዛባም ብሎም ሊሻከርም ይችላል።።ለዚህ የተዛባ
ግንኑኝነት ምንጩ ውዝግብ ነው።በመካከላቸው ጎራ ያስለየ አንድ አወዛጋቢ ርእሰ-ጉዳይ ተገኘ
ማለት ነው።እሱም የራሴ መንግሥት እመሥርታለሁ፣አትመሥርትም ግብግብ ነው እንጂ
በስብስብ መቧደናቸው ወይም ባንድ መንግሥት ራሴን ላስተዳድር ጥያቄው አይደለም መሠረቱ።እሱም
፣በአቅሙ በወጉ ካልተያዝ ማነታረኩ መቼ ይቀራል።

በዚህ ላይ ባህላቸን፤ ሃይማኖታችንና ታሪካችን ሊጠፋ ነው ተብሎ ብሔራዊ ስሜቶችን በማራገብ
የሚደረግ ቅስቀሳና ለፈፋ ይታከልበትና ነገር ዓለሙ ይጦዛል።ተረትና ታሪክ ይደበላለቃል። ማንነትን
ይበልጥኑ የሰው ልጅ ፈጠራ ገፅታው እየጎላ ሲመጣም እንመለከታለን።እዚህ ላይ ቆስቋሹ ከወዝግቡ
ከርዕሰ ጉዳይ ይልቅ ስሜት ቅስቃሽነቱ የየጎላ መመጣቱን መገንዘቡ አይገድም።”ዞሮ ዞሮ ለሰው ወሳኙ
ፖሎቲካዊ ኢድዮሎጂ ወይም የኢኮኖሚ ጥቅማ ጥቅሞች አይደለም።ሰው ሕይወቱን ሰውቶ እስከ ሞት
ድረስ መስዋት ለመክፈል ዝግጁ የሚሆነው ለእምነትና ቤተሰብ ፤ለደም ትሥሥሩና ሚምያምንበት
ጉዳይ ነው፤የሰው ልጅ ወገንተኛነቱን ላረጋገጠለት ቁም ነገር ይዋጋልም ይሞታልም።”(What
ultimately counts for people is not political ideology or economic interest. Faith and
family, blood and belief, are what people identify with and what they will fight and die
for) ይላል ሳሙኤል ሃንቲንግቶን።ሳሙኤል ሃንቲንግቶን ሌላው አስደምዳሚ ነገርም ብሎዋል።
የብሔረሰብና የሃይማኖት ማንነት ዓለማችን ገና ብዙ ያሿኩታሉ ብሎዋል።ሊባኖሳዊ ዝርያ ያለው
በፈረንሳይኛ ፅሓፊ አሚን ማዕልፍ የዛሬ 17 ዓመታት በፃፈው “አገዳዳይ ማንነቶች” በተሰኘው
መፅሓፉም የሚያሰምርበት ይህንኑ ስጋት ነው።መፅሓፉ በኢንግሊዘኛው ትርጉሙ ደግሞ በማንነት
ስም የሃይል ጠቃቀምና ወገንተኛነት ፍላጎት (In the Name of Identity : Violence and the
Need to Belong) ተሰኝቶ ነው በ 1998 የታተመው።

ብሔርተኛነት እንደ ኢድዮሎጂ፤ እንደ እንቅስቃሴና እንደ ስሜት በአመዛኙ ፖሎቲካዊ ክውን
ወይም አሃድ ውጭ ሊታሰብ አይችልም እሰከተባለ ድረስ ከመንግሥት ወይም ብሔር ማዕቀፍ
ውጭ ማሰቡ አስቸጋሪ ነው። ተጋሪዮሽነቱን መሰረት አድርጎ የራሴ ስብስቡ አባላት ባንድ
መንግሥት ትድድር ሥር እንዲጠቃለል የመፈለጉ እንቅስቃሴ አንዱ ነው፡። ስብስቦችን
የሚያፋጥጣቸውና ግብግብ የሚያስገጥማቸው። ይህ በኤውሮፓ ባንድ ታሪካዊ ማጋጠሚያ ላይ
በተጋርዮሻቸው ላይ ተመርኩዘው ያንድ ቋንቋ ተናጋሪ የጠረነፈ መንግሥት የሚመሠረትብት
እንቅስቃሴና አካሄድ ነው።አንዱና ዋነኛው የብሔርተኛነት መግለጫው የራሴ የለውን ስብስብ
ባንድ መንግሥት ሥር መጠርነፉ ፍልጎትና ምኞት ነው።ለኦሮሞ ብሔርተኛነት መንስኤና ሥሮዎ
መነሾ የአፄ ምኒልክ “ወራራ” በቅኝ ግዛት የተያዘችው ኦሮሚያ ነፃ ማውጣት ነው የኦሮሞ ብሔርተኛነት
መደራሻ ግቡ።ታሪክ እንደ መቀስቀሻ የኦሮሞማ ኢድዮሎጂ ደግሞ እንደ ርዮተዓለማዊ አመለካከት
ስንቁ ነው።የማስገበርና የመስፋፋት ዘመቻዎቹን እንደ አካባቢያቸው በቅኝ ግዛት ሥር መውደቅ
ፍልሚያ የሚመለከቱ ወገኖች በታሪኩ ስቆቃነት ብቻ አይደለም የሚከራከሩትና

የሚቀሰቀሱት።ይህ ጭቆና ታሪክ የወደፊት አብሮነታችንን ጭምር አይሞከሬ አድርጎታል ብለው
ሽንጣቸው ገትሮ ይሞገታሉ፣ ብሔርተኞቹ።ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር አኗኗሪ ቀመር ፍለጋ ላይ
የተሰማሩትን በዚህ አይካተቱም።ለኦሮሞ መብት ይሞዋገታሉ እንጂ ለኦሮሚያ ሪፓብሊክ
ምሥረታ አይታገሉምና።የእነሱ ትግል ከቁጫ፣ከዱቤና ከሥልጤ ራስን በራስ ከማስተዳደር መብት
ተለይቶ መታየት ይችላልን?

በእዚህ የሃገራችን የማዕከላዊ ምሥረታ ታሪክ ምዕራፍ ማለት የአፄ ምኒሊክ መስፋፋት
አተረጓጎም ላይ አሁንም ስምምነት እንዳልተደረሰ ለማንም የሃገራችን ጉዳይ ተከታታይ ግልፅ
ነው። ይህም ደግሞ በተራው ይህንን የሃገሪቷ የታሪክ ምዕራፍ በተለየ መልኩ ከሁሉ በላይ
አናታራኪ፣ የክርክርና የእሰጥ አገባ ርእሰ-ጉዳይ እንዲሆን አድርጎታል።
ይህ የኦሮሞ ብሔርተኛነት ሰንበትበት ብሎዋል።መቼ እንደ ተፀነሰ እቅጩን እለት መናገር
ባይቻልም ቅሉ ከአፄ ምኒልክ ግዛት መስፋፋት ጊዜ የተቀጣጠለ የአልገዛ-ባይነት ቀጣይ
እንቅስቃሴ መቼም ልሆን አይችልም። ታዲያ የኦሮሞ ትግል ጅማሮ ብለን የምንፈርጀው ከዬት
ነው?የኦሮሞ ብሔርተኛነት ጅማሮ ክራፕፍ (Krapf) የተባለው የጀርመን ሚስዮናዊ ለኦሮሞ
ግዛት ኦሮማኒያ የሚል ስያሜ በሰጠ ጊዜ ይሁን?።በ 1860 ለኦሮሞ ሕዝብና ሃገር ኦሮማኒያ
የሚል ስም ይስጥ ብሏል የመባሉ ራሱ የኦሮሚያ መፍጠር ፍላጎትና ምኞት ገላጭ ሊሆን
አይችልምና። ታዲያ አናሲሞስ ነሲብ መፅሓፈ ቁልቁሉን (መፅሓፍ ቅዱሱን)በኦሮሚኛ
ከተሮጎሙበት ጊዜ ነው የኦሮሞ ብሔርተኛት የዘፈጥረቱና ጅማሮው ማለቱ ያስኬድ ይሆን?
።ታዲያ ጣልያኖች በ 1935 ኢትዮጵያን ከተቆጣጠሩ ባንድ ዓመት ጊዜ በሃገሪቷ አዲሱን
ክልላዊ አስተዳደር መዋቅር “ጋላና ሲዳማ” ብሎ በምዕራብና በደቡብ የተንሰራፉትን የኦሮም
ግዛቶች ባንድ ላይ ባአጠቃለሉበት ጊዜ ይሁን ወይ?ወይስ በ 1973 የኦሮሞ ነፃነት ግንባር
በተመሰረተበት ዕለት ነው? ወይስ ከዚያ አሥር ዓመት ቀድም ብሎ የመጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበር
በምዕራብ ኦሮሞ የተመሠረተ ጊዜ ነው ፅንሰቱና ውልደቱ? ቀንና እለት መወሰኑ አስቸጋር ነው።
ያም ሆነ ይህ የኦሮሞ ሪፓብሊክ ምሥረታ መዳራሻ-ግቡ ያደረገ ብሔርተኛንነት አለ።ይህ የኦሮሞ
ብሔርተኛ እንቅስቃሴ የኦሮሚያን ሪፓብሊክ ለሃገሪትዋ አንድነት ብሎም ሕልውና የሚደቅነው ስጋት
ከላይ የተመለከተነው የራሰን እድል በራስ የመወሰኑ አተገባበር ውጤት ነው።ይህ ደግሞ ለራሳቸው
ለኦሮሞ ብሔርተኞችና ለነፃነት ግንባር ድርጅቶቻቸው መጋፍጥ የለባቸው ተግዳሮት ነው።አሁንም
እነዚህ ድርጅቶች ቀላል ያልሆኑ ተጨማሪ የቤት ሥራ ከፊታቸው ተደቅኖዋል።ጥቅቶችን
ለመጠቃቀስ፣
· ወደ ቀድሞ ባህላዊ ትድድርና አምልኮ መመለስ (ገዳና ዋቂፌቻ ….ወዘተ የመመለሱ
Rehabilitate ማድረግ ሙከራው)
· ተጠቃሹ ተፎካካር ባላንጣ መቀያየርና መብዛት፤
· የኦሮሙማ ኢድዮሎጂ ትክክለኛ ይዘት አንጥሮ ማውጣት፤
· የኦሮሚፋውና የአማርኛ አጠቃቀምና የረጅሙ ጊዜ ፉክክር
· የሃይማኖታዊ ማንነትና የብሔር ማንነት መጣረዝና መቆላለፍ
· አካአቢያዊና ዓለማቀፋዊ ኩነቶች

ለኦሮሞ ለብሔርተኛ እንቅስቃሴ ተፈታታኝ ተግዳሮቶች የሚደቀኑ ናቸው።ይህንን ሆኔታዎች
የኦሮሞ ምሁራንም ሆኑ የሥልጣን ኤሊቶች ሳይመለከቱቱ ይቀራሉ ብዬ መቼም አልመፃደቅም።ልክ
እንደ ሌላው እነሱንም እንደሚያሳስባቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።ለዚህም ነው በኦሮሞ መብት
ተጋድሎ ስም ከተደራጁት ከደረዝን የሚበልጡት ድርጅቶች አብዛኛዎቹ ያንድ ሃገር ማቀፍ የመረጡት
ወይም በማምረጥ ላይ ያሉት።ደጉ ዜናም እሱ(Good News)ነው።ነፃይቱ ኦሮሚያ ካልተመሰረትች
የኦሮም ጥያቄ እልባት አይገኝለትም ባዮቹ እንዳሉ ተቀበለን ።ስለዚህ የዶር መራራ ጉዲና የአቶ
ቡልቻ ደመቀሳ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ)፣ በጀኔራል ካማል ገልቹ የሚመራው
የኦ.ነ.ግ አንጃ፣ኦፒዲኦ እና የእነ ሌንጮ ለታና የዲማ ነጎዎ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር
(ኦዲግ) በኢትዮጵያ ሃገራዊ ዜግነት መብታቸውን ለማስከበር የሚሹ ናቸው።በዛ ቢል ባንድ
መንግሥት ትድድር ሥር በምን ዓይነት አኗኗር ቀመር አብሮ መኖር እንዳለብን ዳግም
ተወያይተን መስማማት አለብን የሚል ሓሳብ የሚያቀርቡ

አይታጡም፣ከመሃከላቸው።”ኢትዮጵያዊነታችን እንደራደር” አባባልም ለእኔ ከዚህ የዘለለ ትርጉም
አይሰጠኝም።ከመገንጠል ኢትዮጵያን እንዳለች “ኦሮሚያ” እንበላት ባዮችም አሉ።ማን ቀረ? በቅርቡ
ነፃነታቸውን የተቀዳጁት ጎርቤት ኤርትራና ደቡብ ሱዳን እንደ ምሳሌ የሚመለከቱና የኦሮሚያ
ካርታ፣ባንዴራ መልክ መልክ ይዛዋልናል የቀረን ነፃነታችን ማወጅ ብቻ ነው የሚሉ ብሔርተኛ ወገኖች
ናቸው።

ይህንን ፅሑፍ ከማጠቃለሌ በፊት ግን የኦሮሞ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ መጋፈጥ ይኖርበታል ያልኩት
በርካታ ተፈታታኝ ተግዳሮቶቹን እዚህ ማፍታታት ባይቻልም ሰሙነኛ መነጋጋርያ አጄንዳ የሆነውን
የሃይማኖታዊ ማንነትና የብሔር ማንነት መጣረዝ መመልከት አለብኝ። ኦሮሞ በሃገሪቷ ደረጃ አብላጫ
ቁጥር ያለው ስብስብ ብቻ ሳይሆን አብላጫ የሙስሊም አማኞች ያቀፈ ብሔረስብ ነው መባሉ አዲስ
ነገር አይደለም።በሌላ አነጋገር ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኦሮሞዎች ሙስሊሞች ናቸው።ተክክለኛው
ቁጥር ቢዋዥቅም ቅሉ አሮሞ ከፍተኛ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ወይም በሌሎቹ አብላጫው የሙስሊም
ሃይማኖት አማኞች በውስጡ ያካተተ ማሕበረሰባዊ አሃድ መሆኑ ካቶ አያጠያይቅም።ነበር ሊበል?
የኢትዮጵያ ሕዝበ-ሙስሊሙ የወደፊቱ አቅጣጫ የሚወስኑት የኦሮሞ ሙስሊሞች ናቸው ቢባል ማጋነን
አይሆንም ።ባላቸው ቁጥር።አዲስ ክስተቱ ግን በቀርቡ በማንነት ሳቢያ የቁጥር ወይም የአሓዞች ጦርነት
የተጀመረ ይመስላል። ሰለ ተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች የማይስማሙ አመለካከቶች ቢኖረን ከቶ አይገርምም።
አንድ አሓዛዊ መረጃን አስመልክቶ ይህንን ያህል የሚራረቁ ስብጥር መቅረቡ ግን ሳያስተዛብ
አይቀርም።አማሓራ በአመዛኙ ክርስትያን ነው፣እንዲሁም ትግራዊ።አያከራክርም! እስካሁን ሊበል?
እንዲያውም አማራ የሚለው ስያሜ ለክርስይትያን ለተሰኘው አቻ ትርጉም ሲንጠቀምበት ለዘመናት
ኖረናል፣ በዘልማድ።የተወሰኑ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው አማሮች በሃይማኖት ሙስሊም አማኖች እንደሆኑ
ዛሬ፣ ዛሬ አያከራክርም።ሶማሌ፣አፋርና ሓራሬ ሙሉ በሙሉ ሙስሊም ናቸው መባሉ ችግሩ ምን ላይ
እንደ ሆነ አይገባኝም።የኦሮሞ ሕዝብ በአመዛኙ ሙስሊም መባሉም እንዲህ የሚያካራክርም
አልመሰለኝም ነበር።በሰሞኑ ክርክር ግን የሁለቱ ሃይማኖቶች አማኞች እኩል እንደሆኑ አንድ የቀደሞ
የአዳማ ዩኒቭርስቲ ፕሮፌሰር አረጋገጡ ተባለ።ያውም ክርስቲያ ወገን የሆነው ኦሮሞ ባንድ ፐርሰንቴጅ
ልቆ፣ ስብጥሩ 48 በመቶና 47 % ሆነ ተገኘ።ሌላው ተናጋሪ ደግሞ ከኦሮሞ ሕዝብ 80 % ሙስሊም
ነው ብሎ አፉን ሞልቶ ተናገረ።ተወናበደን!ጎበዝ በአመለካከት መለያየት እንችል ይሆናል ነገር ግን
በእስታተስቲካዊ አሓዝም ጭምር ይህን ያህል መወዛገቡ ግን ጉንጫ አልፋ ክርክር ነው።
የዛሬው የኢትዮጵያ ሙስሊሙች መነቃቃትም ያለ ኦሮሞ ሙስሊምች ንቁ ተሳትፎ ትርጉምና ሃገር-
አቀፍ እንደምታና አስተጋቦኦት ሊኖረው አይችልም ቢባል አሁን ምንም ማጋነን የለበትም።ባለፉት 22
ዓመት በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቃተ ሕሊና የተካሄደው ሃያማኖታዊ መነቃቃት፣ በውስጣዊ
ዳይናሚክስ እና በአካባባያዊና ዓለም አቀፍ ሆኔታዎችና ተፅእኖ አዲስ ማንነት የተገነባ ነው
ብለናል።በሃገራችን እስካሁን በሰፈነው የማንነት ፖሎቲካ የብሔረሰብ ማንነት ከሃይማኖታዊ ማንነት

የላቀ ወሳኝ ሚና እንዳለው አያጠያይቅም ።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሃይማኖታዊ ማንነት ለብሔረሰባዊ
ማንነት እየተፎካከረ መሆኑን ልብ ማለታችን አይቀርም።ባንፃሩ ከብሔረሰባቸው ይልቅ ዲናቸውን
(ሃይማኖታቸውን) ቅድሚያ የሚሰጡ ወገኖቸ እየተባራከቱ፣በዚያኑ መጠን የብሔረስብ ማንነት
ትርጉምና ግምት እየቀነሰ የመጣበት ሆኔታ እንመልከታላን።ምክኒያቱ እምብዛም
አያመራምርም።የሃይማኖት ፅንፈኛነት እየፈረጠመ በመጣ ቁጥር በዓለም ፍፃሚ የምፃዓት (የሒሳብ)
ቀን “አላህ ለሙስሊሙ ወንድምህ ምን ሠራህ ብሎ ይጠይቀኝ ይሆናል እንጂ ለኦሮሞ ምን ሥራህ ብሎ
አይጠይቀኝም ” ያለው የሙስሊም አማኝ አክቲቪስት ዓይነቱ ግለሰብ የተኛውን ማንነታቸውን
እንደሚያስቀድሙ አነጋጋሪም፣ አጠያያቂም አይደለም።

እስላም እንደ አንድ ሁሉን-ጠቅለል የእምነት ዘይቤ በመሠረቱ ለማኛውም ብሔርተኛ ዝንባሌ ራሱ
ተፈታታኝ ተግዳሮት ነው። ለኦሮሞ ብሔርተኛነትም እንዲሁ መጋፈጥ ያለበት ተፎካካሪ አስተሳሰብ
ነው።ከዚህ በፊት የብሔረስብ ማንነት የተቆናጥጦት የነበረው አሁን ደግሞ ሃይማኖታዊ ማንነት
ቦታውን እየተቆጣጠረ መምጣቱን ልብ ማለት የግድ ተመራማሪ መሆን አይይሻም እላለሁ። ይህ ደግሞ
በተራው በአሮሞ ብሔርተኛነት ላይ የራሱ ተፅእኖ ማሳረፉ አይቀሬ ነው።የግድ ማለቱ
ይቀለል።እያሳረፍም ነው። ሙስሊማዊ ግዴታቸውን የሚያስቀድሙ ሙስልም ኦሮሞዎች እስከ
ተበራከቱ ድረስ።በሌላ በኩል በኢትዮጵያ እስላማዊ መነቃቃቱ አዲስ የሕዝበ ሙስሊሙ ማንነት ያለ
ኦሮሞ ሙስሊም ግንባር ቀደም ተስትፎ ማሰቡ ዘበት ያደርገዋል።የኦሮሞ ብሔርተኛነት ከሃይማኖታዊ
ሙስለማዊ ማንነት ጋር ውድድር ውስጥ ገብቷል ቢባል ብዙ ማጋነን የለበትም።ከአሮሞ ብሔረሰብ
አብላጫው ክፍል በምሥራቅና በምዕራብ የሚኖረው በእምነቱ ሙስሊም የሆነው ክፍል ነው። የኦሮሞ
ብሔርተኛነት ከወቅታዊ ሙስሊሙ መነቃቃት ጋር ያለው ተያያዥነት ፤ በአውንታዊ ሆነ በአሉታዊ
መልኩ አሻራ ማሳደሩ አይቀሬ ነው።ይህንንም የግድ በግምት መወሰድ ሊያስፈግ ነው።ይህ ደግሞ
ለብሔርተኞቹ አሉታዊ ጎን አያጣም። ቅድሚያ ለሃይማኖቱ ወይም ዲኑ የሚሰጥ ከሆነ ሃገራዊ ወይም
ብሔራዊ ማንነቱ ላይ ሊያስርፍ የሚችለው ጫና አለ።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ማንነት በብሔረሰብ
ማንነት ላይ የበላይነት እየተቆናጠጠ መምጣቱን መካድ የማይችል እውነታ ነው። እስልምና የአማኞቹ
ወንድማመችነት ሰለሚሰብክና ሰለሚያስቀድም።ሁለቱ ማለት እምነትና ብሔርተኛነት ይጣረዛሉ፣
ይወዳደራሉ።አንዱ ሌላው ላይ የበላይነት ለመቀዳጀት።ዲኔን(ሃይማኖቴን)አስቀድማለሁ ፤ ብሔሬን
አስቀድማለሁ ባዮቹ መካከል በሚጧጧፈው ግብግብ ነው።እነዚሁን አስታርቆ መጓዙ ፖሎቲካዊ
ብልህነትን ይጠይቃል። ከሁሉም አቀፍ ኦሮም ብሄርተኛነት ይልቅ የኡማው ወይም የሕዝበ – ሙስሊሙ
መብቶች ማስከበሩ ቅድሚያ የሚሰጠው ደግሞ ለነፃ ኦሮሚያ መሥራቾቹ ተግዳሮት ብቻ ሳይሆን
ከፍተኛ መሰናክል ነው።ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ አንድነት ሃይሎችን ክንድ የሚያጠናክር እንጂ የኦሮሞ
ብሔርተኛነትን አይደለም ። ኦሮሞ እንደ ብሔረሰብ የማስገንጠል ዓላማ ማንገብ ይቻል ይሆናል ነገር
ግን ኢትዮጵያዊ ሕዝበ – ሙስሊሙን አስገንጤ ሙስሊማዊት ኢትዮጵያ እገነባለሁ ፣ማለት
አይቻልም።እምብዛም ልብ አላልነውም እንጂ በሚኖሶታ ስብሰባ ላይ አቶ ነጂብ “ነቢያችን ጎሣኛነትን
አትጠጓት፣ትሸታለች” ብለዋል ማለታቸው ሃይማኖታችን ከአንዱ ብሔረሰብ ወገንተኛነት የሰፋ ነው
ማለታቸው ይመስለኛል። በነገራችን ላይ ይህ የፖሊቲሲዝድ እስለምናና ብሔርተኛነት መካከል
በበርካታ ቦታዎች የተከሰተ አለመጣጣም ነው።ጥሩ ምሳሌው የጃማል አቡዱል ናስር ሥርዓትና
የሙስሊም ወንደማማቾች ደም አፋሳሽ ቅራኔና ግጭት ነው።እስከ ዛሬ በግብፅ ምድር
የሚጧጧፍ።ፖሎቲካል እስላም ኦሮሞ ብሔረተኛነትን ለራሱ ዓላማ መጠቀም ይፈልጋል ወይ? ከሆነ
ጥያቄው፣ መልሱ አዎን! ።በተገላቢጦሹ የኦሮሞ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ሙስሊማዊ መነቃቃትን
መፈናጠጥ(ባንዳንዶቹ አባባል መጥለፍ) ይሞክራል ወይ? ከሆነ መለሱ! አሁንም በሚገባ አዎ፣
ይሞክራል ነው። የተወናበድኩት እኔው ነኝ ወይስ የቁጥር አክሮፓቲስቶች ናቸው?።ኦሮሞ ከኢትዮጵያ
ሕዝብ አንድ ሦስተኛ ከሆነ፣ ሙስሊሙም ሌላው አንድ ሦስተኛ ከሆነ ባንድ ላይ ሲደመር ሁለት

ሦስተኛ ይሆናሉ ብለው የፈነደቁት ናቸው ወይስ በስጋት የተዋጡ ወገኖች? ሁለቱም በዚህ አስገረሚው
የሒሳብ ስሌት ስህተት ሳይሆን አይቀርም። የፈነደቀውም፣የሰጋውም ምክንያትነት ይጎድሎዋል።ተረጋጉ!!
በቀድሞ የአዳማ ፕሮፌሰር እንዳስገነዘቡት የአሮሞ ሕዝብ የእምነት ስብጥሩ አምሳ በአምሳ (Fifty-
Fifty) ሆኖ ከተገኘም ከሙስሊማዊ ፅንፈኛ አስተሳሰብ ሚዛኑን የሚያስጠበቅ ሃይል መኖሩ ተረጋገጠ
ማለት ነው።እስከ ቅርብ ጊዜ ድርስ የኦሮሞ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ አንቀሳቃሽ ሞቶሩ የወለጋ
ፕሮተስታንት ሚሸነሪ ተጠማቂዎች ብለን ስንከሳቸው አለነበረም ወይ?እነዚያም እኮ አሁንም በአመራር
አሉ።አቦ ዳውድ ኢብሣ የክርስትና ስሙ ፍሬው ኢብሣ መሆኑም አንዘንጋ።
በነገራችን ላይ፣ እስላም ሃይማኖትን የማደራጃ መርህ አድርጎ የተንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነፃነት እስላማዊ
ግንባር (Islamic Front for Liberation of Oromia-IFLO) በሟቹ ጃራ አባ ገዳ (አብዱልካሪም
አህመድ ኢብራሂም) ከተቋቋመ ሰበትበት ያለ የኦሮሞ ብሔርተኛ ድርጅት ነው።እኔ እስገባኝ
ድረስ፣የግንባሩ አደረጃጀት መርሑ ነው እንጂ ሙስሊማዊ ፣ እስላማዊት የሆነቸው ኦሮሚያን
ሪፓብሊክ ምሥረታ መዳረሻ ግቡ አድርጎ ቢነሳ ኖሮ ከሌሎቹ መሰለ የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር ከቶ
መተባበር አይችልም ነበር።እንዲያውም በቅድሚያ ቅራኔ፣ በቅራኔ የሚገባው ካንድነት ሃይሎች ጋር
ሳይሆን ደርዘን ከሚቆጠሩት የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባሮች ጋር በሆነ ነበር።የጃራ IFLO ግን የተባበሩት
የኦሮሚያ ነፃነት ሃይሎች (United Forces for Liberation of Oromia-UFLO) አባል ድርጅት ነው።
ማጠቃሊያ
ከማንነቶች መራኮት ወደ አሳባሳቢ ማንነት የሚወሰደን መንገድ ረጅምና ወሰብስብ ነው።ሰሞኑን
የተያያዝነው እስጣ አገበዎች፣ መወራረፎች ወደዚያ የሚያመሩን አይመስለኝም።ከዚህ ጠለቅ ያሉ ረጋ
ያሉ የሓሳብ ልውውጦች የግድ ይላል።ከአንጀት ካለቀሱ እንደሚባለው የሥልጣን ኤሊቶቻችንና
ምሁራኖቻችን ተጨንቀው፣ተጠበው የአእምሮ የደቦ ሥራ ሰርተው ከጦር ከተት ይልቅ የአእምሮ ክተት
ማወጁ የግድ እያለ መጥቶዋል። .ሁሉም ከመካሰስና ከመወራረፍ ባሻገር ለውይይቱ የበኩሉን ድርሻ
የሚወረውርበት የጭንቅላት ደቦ ርብርቦሽ።እኔም በአል ጃዚራም ሆነ በሚኖሶታ ስብስባ በተባሉት
የሚያራርቁ እንጂ ለመግብባት የማይረዱ አባብሎች ላይ አላተኮርኩም።መወገዝ ያለባቸው ትንኮሳዎችን
እንደነበሩ አልሳትኩም።ሰለ እነሱ በፅሑፌ መግቢያ ላይ እንዳልኩኝ ብዙ፣ ብዙ ተብሎዋል።ቀጥታ
በስተሆዋላ ወደ አሉት ጉዳዮች ዝልዬ የገባሁት ለዚሁ ነው።አንድ ተጨማሪ ምክንያት
አለኝ።የአክልዳማ ፊልም ዳረክተሮች ምን ሠርተው ይብሉ? ብላችሁ ነው።ሰሞኑን ቅንብራቸው
መመልከታችን አይቀርም፣ መቼም።የሚያስቆጨው እኛውን ራሳችን ለእነሱ ልጠቀሙበት የሚችሉት
የፊልም እስክርፕት ማቴሪያል ማቀበላችን ነው።ሃይማኖትና ፖሎቲካ (በተለይም እስላም)
ሲጣረዙ(ሲቀሳሰፉ፟?) በሌላ ፅሑፍ በሰፊው እመለስበታለሁ ብዬ ነው እዚህ ላይ ብዙ ሓተታ ውስጥ
ያልገባሁት።
“አሳባሳቢ ማንነት” ደግሞ ምን ያህል ውስብስብነቱ ድርብ ድርብርብ ሊኾን እንደምችል
መገመት አዳጋች አይሆንም ።ባጭሩ፣ በረካታ ማነቶችን ባንድነት አንድ ላይ አቁላልቶ፤አዋህዶ
የሚያስተፃምር ብቻ ሳይሆን ያለፉትን ስህተቶችን ተቀበሎ፤ኢማዕከላዊነት እንደ መርህ አስርፆ፣
የፈዴራል ሥርዓቱን እስካሁን ከታዩት ሕፀፆችን በማፅዳት፣ክልሎችን መልክ ማስያዝ፤በዛሬ
በኢማዕከላውነት አደረጃጀት አማካኝነት የተጎናጸፉትን የራሳቸውን አካባቢያው ችግር በራሳቸው
ጥረቶች መፍታት ሙከራዎቹ ማጎልመስ እንጂ አለመኮሰስ፤ እንደገና ወደ አንድ-ወጥና የጥንቱ
የተማከለ አደረጃጃት መመለስ መሞኮሩ ልያስከተልው የሚችለው ችግር ከወዲሁ በግምት
መውሰድን ያካትታል።በኢትዮጵያ አንድነት ፍፁምነት ስም የተማከለ አደረጃጀት ዳግም አማራጭ
አይሆንም።ኢማዕካላዊ አሥራር ራሱ የዲሞክራሲያዊነት አገባባ አካል ነው።በደረጃውና ያስተዳደር
ጠገጉ ሁሉም የራሱን ጉዳይ በራሱ የሚያስተዳድርበት አግባብ ነውና።የቁጫ ፣ የዱቤና ከዚያ
በፊትም የሥልጤ ማንነት ረፈረንዱም ጉዳይ ከቆብ ያልተቆጠሩት አንዱ ክፍለ ሕዝብ ራሱን
በራሱ የሚያሰተዳድርበት ማካኒዝም ተደረጎ ሰለተቆጠረም ጭምር ይመስልኛል። ባንድ አብሁርታዊ
(ባለ ብዙ ብሔር) ሃገር ከትልቁ አሃድ እስከ ትንሽዋ ወረዳ ራሱን በራሱ የማስተዳደር
ዲሞክራሲያው አግባባ ሆኖ ሰለታየንም ይሆናል።እነ ጀረመን በፈዴራላዊ ሥርዓት የተዋቀሩት የተለያዩ
ቋንቋ የሚናገሩ ብሔር፣ብሔረሰብና ሕዝቦች ኖራቸው አይደለም።ሁሉም የራሱን ጉዳይ በዲሞክራሲያዊ
አግባብ በራሱ እንዲያስተዳድር ነው እንጂ።
አብዛሕነት ተቀብሎ፣ አብዛሕነትን አስተዳድሮ ለዜግነታዊ መንግሥት መሠረት መጣል ምርጫ
የሌለው አማራጭ ነው።ሁሉንም ተቆራቋሽ ገባር ማንነቶች የሚያቀናጅ ሃገራዊ አሰባሳቢ ማንነት
ማስፈለጉ እፅነኦት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ማንነት ለይታና ወገንተኛት እየተብላላ መጥቶ አንዱ ለራስ
ስብስብ ብቻ ወገንተኛቱ ሲያረጋግጥ ማንነት ውዝግብ ሆኖ አቧድኖን ጎራ አስለይቶ ግብግብ
ሲያጋጥመን ጦር እንማዘዛለን።ባንፃሩ አፋቅሮን በመፈክር እንደሚንለው ” ልዩነቶቻቸን ውበታችን
Our Diversity Is Our Beauty ” የተሰኘው ብርቄ የደርገና የኢሕዴአግ የፈረንጅ ተውሶ መፈክር
ተግባራዊንቱ ይረጋገጥና ጎራማሌነታች እንደ ጌጥ ታይቶ አበልፃጊ ብሔራዊ ጥሪታችን ይሆናል።ቁም
ነገሩ ማስተናገዱም ሆነ ማስተዳደሩን ካልቻልንበት (ልክ ሌሎቹ እንደቻሉበት) ጌጦቻችን ሳይሆኑ
የውዝግብ መነሻ ይሆናሉ።በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ የዛሬ ዓመት በፊት የፃፍኩት ወርቀት
ብጤ(ልዩነቶቻችን ውበታችን የሚሆኑት ሲናስተናግዳቸው ብቻ ነው፤ አለበለዚያ ያወዛግቡናል- አፕሪል
2012) ውስጥ ሰፋ ብሎ የተባራሩ ናቸው።በቅድሚያ ልዩነቶቻችን አስተናግደን ማስተዳደር ሲንችል
ብቻ ነው ለዜግነታዊ መንግሥት መሰረት የምንጥለው።እሱም ተግባራዊ የሚሆነው ገባር ወይም
ቅርንጫፍ ማንነቶችን በአስብሳቢ ማንነት ማቀናጀት ሲንችል ነው። የዜግነት መብት ማዕከል ያደረገ
አሰባሳቢ ማንነት ብቻ ነው እነዚያ የተመለክትናቸው አነታራኪ የሆኑትን የቅርንጫፍ ማንነቶቻችንም
ሁላ አዋህዶ ልያስተሳስረን ብቃት ያለው። ኢትዮጵያ እንደ ሃገር፣ የኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ
ባንድነት የሚያኗኑረን ቀመር ካለም እሱ ነው። እጣ ፋንታችንም እሱ ነው፣ ማለት ሳይሻል አይቀርም ።
ዬተኛው ዘር ፣፣ ጎሳ፣ ነገድ፣ብሔር፣ብሔረሰብ፣ዘውግ፣ ወገን ወዳር ተገፋሁ፣ተበድልኩ፣ የሚገባኝን
የሃብትና የሥልጣን ድርሻዬን አላገኘሁም ብሎ መማረርም ሆነ ከነአካቴው ብሶት አልስችል ብሎ አመፅ
ወልዶ ይህንን ለማስተካከል ሸፍቶ ሥልጣንን ለሕዝብ ብሎ ሲቆጣጠር በቀላሉ የሚስተካከል
አለመሆኑን በለፉት 22 ዓመታት ተመልክትናል።በሌላ በኩል የራሴን መንግሥት ካልመሠርትኩ ይህ
በድል ከቶ ሊስተካከል አይችልም ወደ ሚለው መደምደሚያ ደርሶ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን
መብቱን ተግባራዊ አተገባበር መዘዞች በከፊል የስጋት ምንጫችን ሆነው ቁጭ አሉ ከላይ በስፊው
እንደተመለከተነው። ላለፈው 40 ዓመታት በኤሊቶች(የሥልጣን ሊሂቃን?) መካከል የተካሄደው
ክርክር፣ሙግት፣ እሰጣ-አገባ ሆነ አልፎ ተርፎ የመሸነጋገል ስምምነቶች በኢትዮጵያውያን ማህበረሰቦች
ማሃል ፍትሓዊ የሥልጣንና የሃብት ድልድል አላሰፈኑም።”የብሔር ጥያቄ” የተሰኘው ጉዳይ ሁነኛ
መፍትሔ አላተበጀለት።ለዚህም አሁንም የሚያወዛግበን፣ የማንነት ፖሎቲካ ተሰኝቶ።
ባንድ ሃገር ልጅነት (ዜግነት) ተጋሪዮሽ ላይ የተመሠረተ አሳባስቢ ማንነት ሲንል ሰለ ዬተኛው ሃገር
እንደ ምንነጋግር በማንም ዘንደ ብዥታ ሊኖር አይገባም።ኢትዮጵያ ሰለ ተባለችው አንድ ሃገር ነው።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያዊነት እንዳንድ ሃገራዊ አሳባሳቢ ማንነት ሆነ እንዲያያስተሳስርን ስፋትና ብቃት
እንዲኖረው ከተፈለገ ዘንዳ ትክክልኛ ርዮተዓለማዊና ቅርሰ – ውርሳዊ እሴቱ በውልና በቅጡ መታወቅ
ሊኖርበት ነው። ይህ የሁላችን የቤት ሥራ መሆን ይኖርበታል። ትክክለኛው ኢድዮሎጂያዊ ይዘት በውል
ያልተብራራ ገባር ማንነቶችን ደፍጣች የሆነ ኢትዮጵያዊነት ከጥቅሙ ጉዳት የሚያመዝንበት ጊዜ
እንዳአለ መቀበል ሊኖርብን ነው።ብሔርተኛ ኢድዮሊጂ (ለምሳሌ ኦሮሙማ?) ኢትዮጵያዊነትን እንደ
አንድ ሌላ ካልቸራዊ ገዢ መሬት በታሪክ አጋጣሚ መቆጣጠር በለስ የቀነው የአማራ ብሔረሰብ ይህንኑ
ውርስ-ቅርሳዊ በላይነቱን ለማስቀጠል የመሽግበት ሌላ ተፎካካሪ ባልንጣ (Relevant Other) ብቻ-
እንደሆነ ለተከተዮቹ ማሳመን ከቻለ ጉዞችን ይብልጥኑ ይወሳሰባል፣ ያል ጥርጥር። ወቅቱ ያልተኳኳሉ
እውነታዎችን መነጋሪያ ዘመን ነው ብለናል። የአማራ ምሁራንም ሆኑ የሥልጣን ኤሊቶች አማራዊ
ባህላዊ ቅርሰ – ውርሳዊ ማንነትን ከአሰባሳቢው ኢትዮጵያዊ ማንነት መለየቱ ጊዜው የግድ ማለቱን
መገንዘብ ይኖርባቸዋል ። ሰለ አማራ የተባለው ብቻ የሚመለከተውና የሚጎረብጠው መሆኑን በተግባር
እያስመሰከረ ተመልሶ እሱ ብቻ የነቀ፣የበቃና ዝልዝል ማንነቶች ንቆ ፣ልቆና መጥቆ ተረማመዶ
(Transend) በሄደ ልዕለ-ሃገራዊ ኢትዮጵያዊነት (Super Ethiopianism) ባለቤትነቱ የሚመፃዳቅ
ወገን ለዚህ መወሳሰብ ተባብሪ ነው፣ በእኔ እይታ።የኢትዮጵያ ማቀፍ እንደ አኗኗሪ ፎርሙላ
የተቀበሉትም ሆነ ወደዚያ በማምራት ላይ ያሉት ላይ የኦሮሞ መብት ታጋዮቹ ላ ጣት መቀሳሰሩ
አያዋጣም። ለሚደረሰው የማንነት ምስቅልቅል እኩል ተጠያቂ ያደርጋል እንጂ።ወያኔም በእሱ ብሶ፣
ሌላውን “ጠባብ ብሔርተኛ” ብሎ እንደሚከስ አንዘንጋ እንጂ ወገን!
ይህ ኢትዮጵያ በምን መልኩ ትተደዳር ፣ የሃብትና የሥልጣን ድልድል በመንግሥት አወቃቀር በምን
መልኩ ይደራጅ የሚለው ጥያቄ ሁሉን በሚያግባባ መልኩ ተገቢ እልበት ሳያገኝ ቀርቶ ውዝግቡ ወደ
እርስ በእርስ መተላለቅና ፍጅት ካመራ በመሃለችን ከተጠያቅነት የሚያመልጥ ወገን አይኖርም። የእርስ
በእርስ ፍጅትና መተላለቅ አብነቶች በርካታ ናቸው፣መማመሪያ ካስፈለገን።አስፈሪው አስረጅ ምሳሌ
የዛሬዬቱ ሶሪያ ናት።ከዚህ ይሰውርን! እንኳን እኛን ጠላቶቻችንም ይሰውርልን።እንዳንድ ጊዜ አለ!
ጣለትክን የሚያስመርቅ፣ ገጣሚው እንዳለው።ማን ነበር? ጠላቴን ሲመርቅ የተሰኙ ሲኒኞች
የቋጠረው? ታገል ሰይፉ ወይስ በእውቀቱ ስዩም?
ጦቢያ ትባል በነበረቸው በሃገር ቤትዋ መፅሄት ሓሰን ዑመር ዓብዳላ በሚል የብዕር ስም በምፅፍበት
ዘመን አንባቢዎቼ እንደሚያስታውሱት ከእነሱ ጋር ለመጋራት የምጠቃቅሳቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ
ብሔረሰቦች መሳጭ ምሳሌዎችና አባባሎች ነበሩ።የተኞቹ ትግሪኛ ተናጋሪዎች እንደሆኑ አቶ አባተ ኪሾ
እንዳለው እነሱ ይወቁት እንጂ ትግሪኛ ተናጋሪዎቹ አንድ መሳጭ አባባል ነበራቸው። ምን ይላሉ
መሰላአቸሁ ስተርቱ? ”መለበሚ አይትኽላና፣ መለቢሚ ግና አይትግበረና” ይላሉ። ወደ ጥሬው አማርኛ
ሲመለስ፣ የመማመሪያ አብነት አታሳጣን እንጂ እኛኑ መማመሪያ አታድርገን ነው።እኛኑ መቀጣጫ
አብነት ለሌሎች አታድርገን እንጂ ልብ መገዣ ትምህርትማ አትከልክለን ነው፣ በሌላ አባባል። ከሰው
አበሳ ትምህርት መመሩ ብልህነት ነው።ለሌላ ሰው መቀጣጫ ትምህርት መሆን ግን መቅሰፈት
ነው።ከዚህ ሰውረን!!